እስራኤል 300 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን ከራፋህ መውጣታቸውን ገለጸች
"በየሄዱበት ሞት የሚከተላቸው" ፍልስጤማውያን ከደቡባዊ ጋዛ እና ሌሎች አካባቢዎች በፍጥነት እንዲወጡም አሳስባለች
የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ ከወደ ራፋህ የሮኬት ጥቃት መፈጸሙም ተገልጿል
300 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን ከምስራቃዊ ራፋህ መውጣታቸውን የእስራኤል ጦር አስታወቀ።
ጦሩ በዛሬው እለት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ፥ ፍልስጤማውያኑ ወደ “አል ማዋሲ” እና ሌሎች ጊዜያዊ ማረፊያዎች እያቀኑ መሆኑን ጠቁሟል።
ከሰኞ ጀምሮ ፍልስጤማውያን ከራፋህ እንዲወጡ የሚጠይቁ ጽሁፎችን ከአውሮፕላኖች ላይ የበተነችው እስራኤል፥ ከራፋህ ባሻገር ንጹሃን የሃማስ ታጣቂዎች መሽገውባቸዋል ካለቻቸው የጃባሊያ የስደተኞች ጣቢያ እና ከሌሎች 11 አካባቢዎች እንዲወጡም አሳስባለች።
ሃማስ ከራፋህ ያስወነጨፋቸውን አራት ሮኬቶች መትቶ መጣሉን ያስታወቀው የእስራኤል ጦር፥ በምስራቃዊ ራፋህ የሃማስ ይዞታዎች ላይ ድብደባው መቀጠሉን አስታውቋል።
የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር በበኩሉ በእስራኤል የአየር ድብደባ 37 ንጹሃን መገደላቸውንና የሟቾቹ ቁጥር 34 ሺህ 971 መድረሱን መግለጹን ሬውተርስ ዘግቧል።
የአሜሪካና የአለማቀፍ የረድኤት ተቋማት ማስጠንቀቂያን ወደጎን ያለችው ቴል አቪቭ ወታደሮች እና የጦር መሳሪያዎቿን ወደ ራፋህ ድንበር አስጠግታለች።
ለፍልስጤማውያን ሰብአዊ ድጋፍን ለማድረስ ወሳኝ የሆኑት የራፋህ እና የከረም ሻሎም መተላለፊያዎች እንደተዘጉ ናቸው።
ሃማስ ባለፈው ሳምንት በግብጽ እና ኳታር አደራዳሪነት የቀረበውን የጋዛ ተኩስ አቁም እቅድ ተቀብያለው ባለ ማግስት እስራኤል በራፋህ የምድር ውጊያ ለመጀመር ስታደርገው የቆየችውን ዝግጅት ይበልጥ ማጠናከሯ ተገልጿል።
ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያን በተጠለሉባት የዳስ ከተማ ስታካሂደው የቆየችውን የአየር ድብደባ በእግረኛ ጦር በመደገፍ ሃማስን ሙሉ ለመደምሰስ የያዘችው እቅድን ተፈጻሚ ለማድረግ ተቃርባለች።
ከራፋህ የወጡ ፍልስጤማውያን ጊዜያዊ መጠለያዎቹ የእስራኤል ድብደባ ኢላማ መሆናቸው እንደማይቀር ያምናሉ፤ የራፋሁ ጦርነት ሳይጀመር ወደማያውቁት አካባቢ ለመጓዝ የወሰኑት ለጊዜውም ቢሆን ሞትን ለማምለጥ መሆኑንም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እስራኤል ከራፋህ የምታስወጣቸውን ፍልስጤማውያን መሰረታዊ አገልግሎት በተሟላላቸውና ሰብአዊ ድጋፍ በሚቀርብባቸው ጊዜያዊ መጠለያ እያሰፈረች መሆኑን ከመግለጽ ውጪ ዝርዝር መረጃ አልሰጠችም።