የቱርኩ ኢርዶጋን አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ "የተሳሳተ ስሌት" እየሰራች ነው አሉ
ፕሬዝደንት ኢርዶጋን "የጽዮናውያን ውሸትን" ማራመድ ግጭቱን ከማባባስ ውጭ መፍትሄ የለውም ብለዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/14/243-182140-img-20250214-171000-340_700x400.jpg)
ትራምፕ በ16 ወራት የሀማስ-እስራኤል ጦርነት የወደመችው ጋዛ መልሳ እስከምትገነባ ጆርዳንና ግብጽ ፍልስጤማውያንን እንዲወስዷቸው ጫና እያደረጉ ናቸው
የቱርኩ ፕሬዝደንት ታይፕ ኢርዶጋን የአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ አስተዳደር በመካከለኛው ምስራቅ "የተሳሳተ ስሌት" እየሰራ ነው ሲሉ ተችተዋል።
ፕሬዝደንት ኢርዶጋን አክለውም "የጽዮናውያን ውሸትን" ማራመድ ግጭቱን ከማባባስ ውጭ መፍትሄ የለውም ብለዋል።
ቱርክ የፕሬዝደንት ትራምፕን ሁለት ሚሊዮን ገደማ የፍልስጤማውያንን ከጋዛ የማፈናቀልና ጋዛን የመቆጣጠር እቅድ እየተቃወመች ነው።
በእስራኤል መንግስት ላይ አለምአቀፍ ጫና እንዲደረግ ጥሪ እያቀረበች ያለችው ቱርክ እስራኤል በጋዛ እያረሰች የሚገኘው ጥቃት ከዘር ማጥፋት ጋር የሚስተካከል ነው ብላለች።
"እንዳለመታደል ሆኖ አሜሪካ ስለቀጣናችን የተሳሳተ ስሌት እየሰራች ነው። የቀጣናውን ታሪክ፣ እሴትና የተጠራቀሙ ቅራኔዎችን ከግምት የማያስገባ አካሄድ ተገቢ አይደለም" ሲሉ ኤርዶጋን መናገራቸው ተዘግቧል።
ኢርዶጋን ትራምፕ አዲስ ግጭት ከመፍጠር ይልቅ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ያደረጉትን ቃል በመጠበቅ ለሰላም እርምጃ ይወስዳሉ ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል። በጋዛ ተኩስ ቢቆምም የተዘላቂ ተኩስ አቁም ትክክለኛ ምልክቶች አለመኖራቸውንና ሙስሊሙ አለም በጉዳዩ ላይ በትብብር እርምጃ እንዳልወሰደ ጠቅሰዋል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ በ16 ወራት የሀማስ-እስራኤል ጦርነት የወደመችው ጋዛ እስከምትጸዳና መልሳ እስከምትገነባ ጆርዳንና ግብጽ ፍልስጤማውያንን እንዲወስዷቸው ጫና እያደረጉ ናቸው።
ነገርግን ግብጽና ዶርጃንን ጨምሮ በርካታ የአረብ ሀገራት የትራምፕን ጋዛን የመቆጣጠርና ፍልስጤማውያንን የማፈናቀል እቅድ እንደማይቀበሉት አቋማቸውን ይፋ አድርግዋል።