ኢራን ጠላቶቿ አሁን ያሏትን የኑክሌር ጣቢያዎች ከመቱባት አዲስ ማቋቋም እንደምትችል ገለጸች
የኢራኑ ፕሬዝደንት ፔዜሽኪያን የቴህራን ጠላቶች የኑክሌር ጣቢያዎቿን ሊመቱባት ቢችሉም አዳዲሶች የመገንባት አቅሟን መከልከል አይችሉም ብለዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/14/243-135154-img-20250214-124832-438_700x400.jpg)
እስራኤልና ኢራን ወደ ቀጥተኛ የእርስበእርስ መጠቃቃት የገቡት በጋዛ ጦርነት ከፍተኛ ውጥረት በተፈጠረበት ባለፈው አመት ነበር
ኢራን ጠላቶቿ አሁን ያሏትን የኑክሌር ጣቢያዎች ከመቱባት አዲስ ማቋቋም እንደምትችል ገለጸች።
የኢራኑ ፕሬዝደንት መስኡድ ፔዜሽኪያን የቴህራን ጠላቶች የኑክሌር ጣቢያዎቿን ሊመቱባት ይችላሉ፤ ነገርግን አዳዲሶች የመገንባት አቅሟን መከልከል አይችሉም ብለዋል።
ፔዜሽኪያን ይህን ያሉት ዋሽንግተን ፖስት የአሜሪካ ስለላ ድርጅት እስራኤል በሚቀጥለው አመት አጋማሻ ላይ በኢራን ኑክሌር ፕሮግራም ላይ ቀድማ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች ብሎ ያምናል ሲል መዘገቡን ተከትሎ ነው።
"የኑክሌር ጣቢያዎችን እንመታለን እያሉ እያስፈራሩ ነው። ጠላት ከእነዚህ ውስጥ 100ዎቹን የሚመታ ከሆነ ሌሎች 1ሺ እንገነባለን...ህንጻዎቹንና ቦታውን ልትመታ ትችላህ፤ የገነቡትን ግን መምታት አትችልም" ሲሉ ፔዜሽኪያን ለመንግስት ሚዲያዎች መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እስራኤል የኢራንን ኑክሌር ጣቢያዎች ልትመታ እንደምትችል ጠቅሰዋል። ትራምፕ ይህን ለማስቀረት ከኢራን ጋር የኑክሌር ስምምነት ማድረግ እንደሚፈልጉም ገልጸዋል።
"ሁሉም ሰው እስራኤል በእኛ ድጋፍ ወይም እኛ ካጸደቅንላት ልትመታው እንደምትችል ያስባል። ያ እንዲሆን አልመርጥም" ብለዋል ትራምፕ።
የኢራን መደበኛ አየር ኃይል አዛዥ ሀሚድ ቫሄዲ "ለሁሉም ሀገራት፣ ለወዳጆቻችንና ለጠላቶቻችን የኢራን ፖሊሲ ራሷን መከላከልና መሆኑን አሳውቀናል። ነገርግን ለየትኛውም የጠላት ጥቃት በኃይል ምላሽ እንሰጣለን" ሲሉ ባለፈው ሀሙስ እለት ተናግረዋል።
እስራኤልና ኢራን ወደ ቀጥተኛ የእርስበእርስ መጠቃቃት የገቡት በጋዛ ጦርነት ከፍተኛ ውጥረት በተፈጠረበት ባለፈው አመት ነበር።