ቱርክ እና ግብጽ የንግድ ልውውጣቸውን በ50 በመቶ ለማሳደግ ተስማሙ
ሀገራቱ "የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችል ፍኖተ ካርታ" ላይ ተስማምተዋል
አንካራ እና ካይሮ አምባሳደሮችን በመሾም ግንኙነታቸውን ወደነበረበት ለመመለስ ወስነዋል
ቱርክ እና ግብጽ የንግድ ልውውጥን በ50 በመቶ ለማሳደግ ተስማሙ።
ቱርክ እና ግብጽ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የንግድ ልውውጣቸውን በ50 በመቶ ለማሳደግ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ስምምነቱ የግብጽ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚንስትር አምህድ ሳሚር ሳላህ እና የቱርኩ አቻቸው ኦመር ቦላት በአንካራ ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ይፋ ተደርጓል።
የግብጽ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስቴር በትዊተር ገጹ እንዳስታወቀው ከ10 ዓመታት በኋላ በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረገው የመጀመሪያ ውይይት "የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችል ፍኖተ ካርታ" ላይ ተስማምተዋል።
ሁለቱ ሚንስትሮች በጋራ በሰጡት መግለጫ የጋራ የንግድ ልውውጥን አሁን ካለበት 10 ቢሊዮን ዶላር ወደ 15 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያሳድጉ አስታውቋል።
ሁለቱ ሚንስትሮች እ.አ.አ. በ2005 በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈረመውን ነጻ የንግድ ስምምነት ለመተግበር እና በ2012 ከተካሄደው የከፍተኛ ደረጃ የንግድ ምክክር ቀጣይ ስብሰባ ለማድረግ ተስማምተዋል።
እ.አ.አ. በ2013 ፕሬዝዳንት መሀመድ ሙርሲ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባት ተከትሎ የሁለቱም ውጥኖች እድገት ቆሟል።
የቱርክ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን በራባ አደባባይ የተፈጸመውን እልቂት በመቃወም የግብጹን ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲን አንባገነን ሲሉ ጠርተዋል።
ግብጽ እና ቱርክ በሀምሌ ወር አምባሳደሮችን ሾመዋል።