የዩክሬኑ ተወካይ የሩሲያ ተወካይ ባለስልጣን ላይ ቡጢ ሲሰነዝሩም ታይቷል
የሩሲያ እና ዩክሬን ዲፕሎማቶች በቱርክ ለስብሰባ በሄዱበት ቡጢ መሰናዘራቸው ተሰምቷል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 15ኛ ወሩ ላይ የሚገኝ ሲሆን በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን እያስተናገደ ነው።
አሁን ደግሞ የጥቁር ባህር የኢኮኖሚ ትብብር በቱርክ ሙዲና አንካራ እየተካሄደ ይገኛል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ተወካዮች በዚህ መድረክ ላይ ሀገራቸውን ወክለው እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የዩክሬን ተወካይ በመድረኩ ላይ የሀገሩን ሰንደቅ ዓላማ ይዞ ቆሞ እያለ የሩሲያ ተወካይ ወደ መድረኩ በመምጣት ነጥቆ ለመሄድ ሲሞክር አለመግባባቱ መከሰቱ ተገልጿል።
የዩክሬኑ ተወካይም በሩሲያ አቻው ላይ በቡጢ መምታቱን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በስፋት በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
የቱርክ መንግሥት በበኩሉ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እልባት እንዲያገኝ ብዙ ጥረቶችን እያደረግን ባለንበት ብዚህ ወቅት እንዲህ አይነት ክስተቱ መፈጸሙ ትክክል እንዳልሆነ በሀገሪቱ ፓርላማ ድረገጽ ላይ ይፋ ባደረገችው መግለጫ አስታውቃለች።
የአንካራ ከተማ የጸጥታ ሀይሎችም ወደ ግጭት ገብተዋል የተባሉ የሩሲያ እና ዩክሬን ተወካዮች ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ሩሲያ ከሰሞኑ ዩክሬን በሰው አልባ አውሮፕላን ወይም ድሮን የታገዘ ጥቃት በክሪምሊን ቤተ መንግሥት ላይ ጥቃት አድርሳለች ስትል ከሳለች።
ዩክሬን በበኩሏ ፕሬዝዳንት ፑቲንን ለመግደልም ሆነ በክሪምሊን ቤተ መንግሥት ላይ ምንም አይነት ጥቃት አልሰነዘርኩም ማለቷ ይታወሳል።