የኤርትራው ፕሬዝዳንት ከግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መክረዋል
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከግብጹ አቻቸው አብዱል ፈታህ አልሲሲ የተላከላቸውን መልእክት ተቀበሉ።
የግብጽ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሜህ ሹክሪ የፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲን መልዕክት ይዘው በትናንተናው እለት አስመራ መግባታቸው ይታወቃል።
በትናንትናው እለት ምሽትም የኤርትው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሜህ ሹክሪ የተመራውን የግብጽ ልኡክ ተቀብለው ማነጋገራቸውን የሀገሪቱ ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር አስታውቋል።
በዚሁ ወቅትም የግብጽ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሜህ ሹክሪ ከፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ ኤል-ሲሲን የተላከ ደብዳቤ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አድርሰዋል።
የፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ ኤል-ሲሲ ደብዳቤም “የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ማጠናከር እና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት” ላይ የሚያተኩር መሆኑም ተነግሯል።
የግብጽ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሜህ ሹክሪ በዚሁ ወቅት እዳስታወቁት “የአሁኑ ጉብኝታቸው ሁለቱ ሀገራት መደበኛ ስብሰባዎች አካል መሆኑን እንዲሁም ቀደም ሲል በሀገራቱ መካከል የተደረሱ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን አፈፃፀም ሂደት ለመገምገም ያለመ ነው” ብለዋል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ ከሁለት ቀናት በፊት ወደ ኤርትራ አምርተው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር 20 ኪሎሜትሮች የሚረዝም የባህር ጠረፍ እንድትከራይ እና በምትኩ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ የሚያስችል ነው።
ይህ ስምምነት ሶማሊላንድን የራሷ ሉአላዊ ግዛት አድርጋ በምታያት ሶማሊያ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።
ይህን ተከትሎም ግብጽን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እና ተቋማት የሱማሊያ ሉዓላዊነትን እንደሚያከብሩ ስምምነቱን እንደማይደግፉት የተናገሩ ሲሆን፤ ግብጽም በይፋ ከሶማያ ጎን እንደምትቆም ማሳወቋ ይታወሳል።