ኤርትራውያኑ “እስራኤል ሀገራችን ናት፤ ሁለተኛ ሀገራችን እየደማች አንታገስም” ብለዋል
በእስራኤል የሚገኙ ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች “ሁለተኛ ሀገራችን እየደማች ነው” ሲሉ ተናገሩ።
ሃማስ ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ እና ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የትውልድ አገራቸውን ጥለው ወደ እስራኤል የገቡ ኤርትራውያን ተጨማሪ መፈናቀል ደርሶባቸዋል።
18 ሺህ የሚጠጉ ጥገኝነት ጠያቂ ኤርትራውያን በእስራኤል የሚኖሩ ሲሆን፤ የሃማስን ጥቃት ተከትሎ በድጋሚ ከመኖሪያቸው ለመፈናቀል መገደዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ተክሊት የተባለች ኤርትራዊት ጥገኝነት ጠያቂ፤ ሃማስ ባሳለፍነው ሳምንት እሁድ በተኮሳቸው ሮኬቶች መኖሪያ ቤቷ ሙሉ በሙሉ መውደሙን ትናራለች።
በወቅቱ የነበረው ሁኔታ በጣም አስጨናቂ እንደነበረ ያስታወቀችው ተክሊት፤ “በእግዚአብሄር ጥበቃ ተርፊያለው” ብላለች።
በእስራኤል ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው አሸከሎን ከተማ ለ13 ዓመታት የኖረችው ተክሊት በሃማስ ጥቃት ያላት ንብረት ሙሉ በሙሉ መውደሙንም እታውቃለች።
ሌላኛው ኤርትራዊ ከአሽከሎን ወደ ናታኒያ ከተዘዋወረ በኋላ የሃማስ ጥቃትን ተከትሎ አዲስ ስደተኛ እንደሆነ ያክል እንደተሰማው ተናግሯል።
ቤቴ እና ንብረቴ ሙሉ በሙሉ ወድሟል ያለው ኤርትራዊው፤ ቢያንስ ከአስረፊ ድምጽ ርቂያለሁ፤ አሁን ሰላማዊ ቦታ ነው ያለሁት ብሏል።
የእስራኤል ሃማስን ጦርነት ተከትሎ የተወሰኑ ኤርትራዉያን የገቡበት አይታወቅም ያሉት ኤርትረውያኑ፤ ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅም ከእስራኤል ጦርና ፖሊሶች ጋር እየሰሩ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በእስራኤል የሚኖሩ ኤርትራውያን በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ “እስራኤል ሀገራችን ናት፤ ሁለተኛ ሀገራችን እየደማች አንታገስም” ብለዋል።
ኤርትራውያን እና ሱዳናውያን ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞች ወደ እስራኤል መግባት የጀመሩት በፈረንጆቹ ከ2006 ጀምሮ ሲሆን፤ አብዛኛው ስደተኛ በግብጽ ሲናይ በረሃ በኩል ወደ እስራኤል መግባት እንደጀመሩ ይነገራል።