ኤሪክ ቴን ሀግ ያሰናበተው ማንችስተር ዩናይትድ ሩድ ቫኔስትሮይን ጊዜያዊ አስልጣኝ አድርጎ ሾመ
አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ከ850 ቀናት የኦልትራፎርድ ቆይታ በኋላ ከዩናይትድ ጋር በይፋ ተለያይተዋል
በውጤት ቀውስ ላይ የሚገኝው ዩናይትድ ባለፉት ሳምንታት በሁሉም ሊጎች ካደረጋቸው 9 ጨዋታዎች አንድ ብቻ ነው ማሸነፍ የቻለው
ኔዘርላንዳዊው አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ የ850 ቀናት የኦልትራፎርድ ቆይታ በይፋ መጠናቀቁ ተረጋግጧል፡፡
ለላፉት ሁለት አመታት ተኩል ከእንግሊዝ ትላልቅ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነውን ማንችስተር ዩናይትድ ለ128 ጨዋታዎች የመሩት ቴን ሀግ ከቡድኑ አሰልጣኝነት መሰናበታቸው ተሰምቷል፡፡
ከ2022 ጀምሮ በሀላፊነት የነበሩት አሰልጣኙ በቆይታቸው የካራባዎ እና የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ማሳካት ቢችሉም ባለፈው አመት የነበራቸው አጨራረስ እና ዘንድሮ በሊጉ ባሳዩት አጀማመር በከፍተኛ ጫና ውስጥ ገብተው ቆይተዋል፡፡
ሰር ጂም ራትክሊፍ ባለፈው ክረምት ለአሰልጣኙ ተጨማሪ እድል ለመስጠት የሁለት አመት ኮንትራት አስፈርመዋቸው የነበረ ቢሆንም ቡድኑ የቀጠለበት የውጤት መዋዤቅ ጉዞ አሰልጣኙ እንዲሰናበቱ ምክንያት መሆኑ ተሰምቷል፡፡
በውድድር ዘመኑ መጀመርያ የአሰልጣኙን ኮንትራት በሁለት አመት ያራዘመው የሰር ጂም ራትክሊፍ አስተዳደር ከአሰልጣኙ ጎን እንደሆነ ቢገልጽም ቡድኑ እያሳየ በሚገኘው አቋም ደስተኛ አለመሆኑን የእንግሊዝ ጋዜጦች በተደጋጋሚ አስነብበዋል፡፡
በዝውውር መስኮቱ የቡድኑን ጥልቀት ለማሻሻል በተለይ የአማካይ እና የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ነበር፡፡
በዚህም ከ150 ሚሊየን ፓውንድ በላይ በማውጣት ዩናይትድን ለማጠናከር ጥረት ቢደረግም አሁንም ከውጤት ርቆ በሚዋዣቅ አቋም ውስጥ ይገኛል፡፡
ኔዘርላንዳዊው አሰልጣኝ በሁለት አመት ተኩል የአሰልጣኝነት ቆይታቸው 128 ጨዋታዎችን አድርገው 72 ጨዋታዎችን ማሸነፍ ሲችሉ 36 ጨዋታዎችን ተሸንፈዋል፡፡
በክለቡ በነበራቸው ቆይታም ከእያንዳንዱ ጨዋታ በአማካይ 1.84 ነጥብ ማግኝት ችለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ እስኪሾምለት ድረስ ምክትል አሰልጣኙ የቀድሞ የቡድኑ ተጫዋች ሩድ ቫኒስትሮይ በጌዜያዊነት እንደሚመራ ይጠበቃል፡፡
የእንግሊዙ ማንችሰተር ኢቪኒንግ ጋዜጣ የማንችስተር ዩናይትድን ውጤት ማጣት ተከትሎ ቴን ሀግ የሚሰናበቱ ከሆነ ቀጣዩ አሰልጣኝ ማን ቢሆን ትመርጣላችሁ በሚል ከቡድኑ ደጋፊዎች ድምጽ አሰባስቦ ነበር።
በዚህም ደጋፊዎች ለ9 የተለያዩ አሰልጣኞች ድምጻቸውን የሰጡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ቶማስ ቱህል 29 በመቶ ድጋፍ በማግኝት ቀዳሚው ሆነዋል፡፡
16 በመቶ ድምጽ በማግኝት ሁለተኛውን ከፍተኛ ድጋፍ ያገኝው የቀድሞው የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ዚነዲን ዚዳን ነው።
ቫኒስትሮይ ፣ ማስሚላኖ አሌግሪ ፣ ሲሞን ኢንዛጊ ፣ ማይክል ካሪክ ፣ ግርሀም ፖተር እና ጋሬዝ ሳውዝጌት በተከታታይ ቀጣይ የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ቢሆኑ በሚል ከፍተኛ ድጋፍ ያገኙ ናቸው።
የቀድሞ የቼልሲ አለቃ ቶማስ ቱህል የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን ለማሰልጠን መስማማታቸውን ተከትሎ ከዝርዝሩ ውስጥ ወጥተዋል፤ በዚህም ቀጣይ ዩናይትድን የሚረከበው አሰልጣኝ በቴክኒክ እና በታክቲክ የዳበረ ልምድ ያለው ቡድኑን ማሻሻል ላይ ትልቅ ሃላፊነት የሚጠብቅው ነው ተብሏል፡፡
ባለፉት አስርተ አመታት ውስጥ በእንግሊዝ ፕርሚየርሊግ ፣ በአውሮፓ ሊግ እና ሻምፒዮንስ ሊግ ተፎካካሪ እንዲሁም የሊጎቹም ዋንጫ ባለቤት በመሆን ጠንካራ ክለብ መሆኑን ያስመሰከረው ዩናይትድ ውጤት ከራቀው አመታት ተቆጠሩ።
የቡድኑ የምንግዜም ምርጥ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን መልቀቀን ተከትሎ በ11 አመት ውስጥ ቴን ሀግን ጨምሮ 7 አሰልጣኞችን እና ሁለት ጊዜያዊ አስልጣኖችን የቀያየረው ዩናይትድ የሚፈልገውን ወጥ አቋም እና ውጤት ማስመዝገብ አልቻለም።
በአሁኑ ወቅትም ባለፉት ሳምንታት በሁሉም ሊጎች ባደረጋቸው 9 ጨዋታዎች አንድ ብቻ በማሸነፍ በእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ ደረጃ ደግሞ 14 ተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡