ኤሪክ ቴን ሀግ የማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች እንዲታገሷቸው ጠየቁ
አሰልጣኙ ይህን ያሉት በአውሮፓ ሊግ ጨዋታ ከፖርቶ ጋር አቻ ከተለያዩ በኋላ በሰጡት አስተያየት ነው
የቡድኑ መነቃቃት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ያሉት ቴን ሀግ የተከላካይ ስፍራን ማጠናከር ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል
የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ደጋፊዎች እንዲታገሷቸው ጠይቀዋል፡፡
በእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሶስቱን የተሸነፈው ማንችስተር ዩናይትድ በሊጉ 13ተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
በአውሮፓ ሊግ ግጥሚያ ትላንት ምሽት ከፖርቶ ጋር ባደረገው ጨዋታ ሁለት ለዜሮ ከመምራት ተነስቶ 3ለ3 አቻ ተለያይቷል፡፡
በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከ150 ሚሊየን ፓውንድ በላይ በማውጣት ቡድኑን ለማጠናከር ጥረት ቢደረግም ዩናይትድ አሁንም ከውጤት ርቆ በሚዋዣቅ አቋም ውስጥ ይገኛል፡፡
በዚህ የተነሳም ዩናይትድን አቀናጅቶ መምራት ተስኗቸዋል የተባሉት አሰልጣኝ ከደጋፊዎቹ እና ከተለያዩ የስፖርት ተንታኞች ጫና በርትቶባቸዋል፡፡
ኤሪክ ቴን ሀግ ከምሽቱ የአውሮፓ ሊግ ጨዋታ በኋላ በሰጡት አስተያየት የቡድኑ መነቃቃት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረው ደጋፊዎች እንዲታገሷቸው ጠይቀዋል፡፡
ከጋዜጦች ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ “በዚህ ሰአት እኛን ለመዳኝት ጊዜው ገና ነው፤ መዳኝት እና መወቀስ ካለብን በውድድር ዘመኑ ማብቂያ ላይ ሊሆን ይገባዋል ፤ ቡድኑን እየገነባነው ነው። የቡድኑን አቅም ማደበር ላይ የምንሰራውን ስራ አናቋርጥም ውጤታማ እንደምንሆንም እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የቡድኑ መነቃቃት እና ለማሸነፍ ያለው መነሳሳት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ያሉት ቴን ሀግ በአንዳንድ የአማካይ እና ተከላካይ ስፍራዎች ላይ ማሻሻል ያሉብን ጉዳዮች እንዳሉ ተገንዝበናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በትላንት ምሽቱ ጨዋታ በማርከስ ራሽፎርድ እና በራስመስ ሆሉንድ ሁለት ግቦች ሲመራ የቆየው ዩናይትድ በተከታታይ በተቆጠረበት ሶስት ግቦች ለሽንፈት ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም በጭማሪ ሰአት ሃሪ ማጉየር ባስቆጠራት ግብ አቻ ውጤት ይዞ መውጣት ችሏል፡፡
በእንግሊዝ ፕርምየር ሊግ ውጤት የራቃቸው ቀያይ ሰይጣኖቹ በአውሮፓ ሊግም አምስት ጨዋታዎችን ያለአሸናፊነት አጠናቀዋል፡፡
በውድድር ዘመኑ መጀመርያ የአሰልጣኙን ኮንትራት በሁለት አመት ያራዘመው የሰር ጂም ራትክሊፍ አስተዳደር ከአሰልጣኙ ጎን እንደሆነ ቢገልጽም ቡድኑ እያሳየ በሚገኘው አቋም ደስተኛ አለመሆኑን የእንግሊዝ ጋዜጦች በተደጋጋሚ አስነብበዋል፡፡
ማንችስተር ዩናይትድ በመጪው እሁድ በ7ተኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ ግጥሚያ ሶስት ጨዋታዎችን አሸንፎ አንድ አቻ እና አንድ ሽንፈት ካስተናገደው በሰንጠረዡ 5ተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው አስቶንቪላ ጋር ይገጥማል፡፡