ቴን ሀግ ከካራባዎ ዋንጫ ስንብት በኋላ ምን አሉ?
ዩናይትድ በኒውካስትል በሜዳው 3 ለ 0 ተሸንፎ ከውድድሩ መሰናበቱ በአሰልጣኙ ላይ ተቃውሞውን አብዝቶባቸዋል
ማንቸስተር ካለፉት 10 የኦልትራፎርድ ፍልሚያዎች በአምስቱ በመሸነፍ ከ1930 ወዲህ ደካማ ጅማሮ አስመዝግቧል
ማንቸስተር ዩናይትድ በተከታታይ በኦልትራፎርድ ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ተቃውሞው እየበረከተባቸው ነው።
ዩናይትድ በፕሪሚየር ሊጉ በከተማ ተቀናቃኙ ሲቲ የ3 ለ 0 ሽንፈት በገጠመው ማግስት በተመሳሳይ ውጤት በኒውካስትል ተሸንፎ ከካራባዎ ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ተሰናብቷል።
የኢዲ ሆው ቡድን ስምንት ተጫዋቾችን ቀይሮ ዩናይትድን 3 ለ 0 ማሸነፉ የሆላንዳዊውን አሰልጣኝ የኦልትራፎርድ ቆይታ እያበቃለት መሆኑን ያሳያል የሚሉ አስተያየቶችም ጎላ ብለው እየተደመጡ ነው።
ታዋቂው ጣሊያናዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ፋብሪዚዮ ሮማኖ እንደዘገበው አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ከኒውካስትሉ ጨዋታ በኋላ ለተጫዋቾቻቸው ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በጨዋታው ቡድናቸው ድክመት እንደነበረበት ያመኑት አሰልጣኙ “ሃላፊነቱን እኔም ሁላችሁም (ተጫዋቾቹ) ልንወስድ ይገባል” ነው ያሉት።
“ታጋይ ነኝ፣ ምንም እንኳን አሁን ያለንበት ደረጃ መጥፎ ቢሆንም እርግጠኛ ነኝ አስተካክለዋለው” ሲሉም ተደምጠዋል።
ጤን ሃግ “ክለቡ እያሳየ ለሚገኘው ደካማ ውጤት ሃላፊነቱን እወስዳለሁ” ባሉበት ንግግራቸው ተጫዋቾች በሙሉ ሃላፊነት ተሰምቷቸው እንደ አንድ ቡድን እንዲፋለሙ አሳስበዋል ብሏል ፋብሪዚዮ ሮማኖ።
አሰልጣኙ በፈታኝ ወቅትም ለክለባቸው አጋርነታቸውን እያሳዩ ለሚገኙ የዩናይትድ ደጋፊዎች በቀጣይ በተሻለ ውጤት እክሳለሁ የሚል የይቅርታ መልዕክት ማስተላለፋቸውም አክሏል።
በማንቸስተር ዩናይትድ የ18 ወራት ቆይታ ያደረጉት ኤሪክ ቴን ሃግ በቀጣይ በፕሪሚየር ሊጉ ከፉልሃም ጋር ይጫወታሉ።
ዩናይትድ በ10 ጨዋታ 15 ነጥብ በመያዝ በሊጉ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ቡድኑ ባለፉት 10 የኦልትራፎርድ ግጥሚያዎች በአምስቱ በመሸነፍም ከ1930 ወዲህ ደካማ ጅማሮ አስመዝግቧል።
ይህም በሆላንዳዊው አሰልጣኝ ላይ ደጋፊዎች ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲያነሱ ምክንያት ሁኗል።