ማንቸስተር ዩናይትድ የቡድን ስብስቡን ለማጠናከር የሞትሽረት ትግል ማድረግ አለበት- ኤሪክ ቴንሀግ
አሰልጣኙ የውድድር ዘመኑ ከመጀመሩ በፊት የቡድን ጥልቀት ላይ መሰራት ካልተቻለ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አይቻልም ብለዋል
ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ዩናይትድ 60 ጉዳቶችን አስመዝግቧል
የእንግሊዙ ክለብ ማንቸስተር ዩናይትድ የቡድን ጥልቀት ላይ የሞት ሽረት ትግል ማድረግ እንደሚኖርበት የቡድኑ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴንሀግ አስጠነቀቁ።
የዘንድሮው የዝውውር መስኮት ከመጠናቀቁ በፊት የቡድኑን ስብስብ የሚያጠናከሩ ተጫዋቾችን ማስፈረም ላይ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በትኩረት ካልሰራ የውጤት ለውጥ አይኖርም ብለዋል።
አሰልጣኙ አክለውም “ሁሉም ተጫዋቾች ከጉዳት ውጭ በጥሩ አቋም ላይ ሲሆኑ ጨዋታዎችን እናሸንፋለን ጉዳት በሚያጋጥመን ጊዜ ግን ተጨዋቹን ተክቶ ሊጫወት የሚችል ጥሩ አቅም ያለው ተጫዋች እጥረት ስላለብን እንሸነፋለን” ብለዋል።
በጉዳት መደራረብ ምክንያት ተጨዋቾች ለይ የሚፈጠር ጫና ቡድኑ ውጤት እንዲርቀው ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ዋነኛው ነው ተብሏል።
ቴንሀግ “በስብስባችን ውስጥ አሁንም ጉዳት ላይ የሚገኙ በርካታ ተጫዋቾች አሉ በቅርቡ በሚጀምረው ውድድር ከሌሎች ጠንካራ የእንግሊዝ ክለቦች እኩል ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ ክፍተቶችን የሚሞሉ ተጫዋቾችን ማስፈረም ላይ ልንፈጥን ይገባል” ነው ያሉት።
ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በ8ተኛ ደረጃ ላይ ፕርሚየርሊጉን ያጠናቀቀው ዩናይትድ የተለየ የቡድን ግንባታ እና ጥልቀት ላይ ሊሰራ እንደሚገባ አሰልጣኙ አሳስበዋል።
ቡድኑ እስካሁን በተከላካይ መስመር ላይ ሌኒ ዮሮ በአጥቂ ስፍራ ላይ ደግሞ ጆሽዋ ዚርኪዚን ማስፈረም የቻለ ሲሆን የባየር ሙኒኩን የመስመር ተከላካይ ኑሴር ማዝራዊን እና የፒኤስጂውን ተከላካይ አማካይ ማኑዌል ኡጋርቴን ለማስፈረም ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።
አሰልጣኝ ቴን ሀግ አዲሱ የክለቡ አስተዳደር ተጫዋቾችን ለማስፈረም እና ቡድኑን ለማጠናከር ጥሩ መነሳሳት እንዳለው ገልጸው የቡድን ግንባታ በአንድ አመት ውስጥ ባይጠናቀቅም ነገር ግን ለመጭው የውድድር ዘመን ብቁ የሚያደርጉንን ተጫዋቾች ማሰባሰብ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነው ብለዋል።
ማንችስተር ዩናይትድ ዛሬ ምሽት የቅድመ ውድድር ዘመን የአቋም መለኪያ ጨዋታውን ከአርሰናል ጋር በአሜሪካ ሎስአንጀለስ ሶፊ ስታድየም ያደርጋል።