ማንቸስተር ዩናይትድ 250 ሰራተኞቹን ሊቀንስ ነው
ከዩናይትድ 25 በመቶ ድርሻ የገዙት ሰር ጂም ራትክሊፍ ክለቡ ከውጤቱ አንጻር የተጋነነ የሰው ሃይል መቅጠሩን ያምናሉ
ለአራት ተከታታይ አመት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ያነሳው ማንቸስተር ሲቲ የሰራተኛ ቁጥር ከዩናይትድ በግማሽ ያንሳል
ማንቸስተር ዩናይትድ 250 ሰራተኞቹን ሊቀንስ መሆኑ ተነገረ።
የክለቡ ዳይሬክተር ሰር ዴቭ ብሬልስፎርድ የሰር ጂም ራትክሊፉ ኢኒዮስ ኩባንያ የዩናይትድን 25 በመቶ ድርሻ ከገዛበት ታህሳስ ወር ወዲህ የክለቡን ወጪ ለመቀነስ ሲያጠኑ መቆየታቸው ተገልጿል።
ግምገማቸውም ቀያዮቹ ሰይጣኖች አሁን ካለበት አቋም ጋር የማይጣጣም በርካታ የሰው ሃይል መቅጠራቸውን የሚያመላክት መሆኑን ዘ አትሌቲክ አስነብቧል።
ኢኒዮስ የክለቡን የቢዝነስና የስራ ወጪዎች እንዲያጠና የቀጠረው አማካሪ ኩባንያ ኢንተርፓዝም የሰው ሀይል አስተዳደሩ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው ምክረሃሳቡን አቅርቦ ነበር።
በትናንትናው እለት ይፋ የተደረገው የሰራተኞች ቅነሳ ውሳኔ ከውጤቱ አንጻር የተጋነነ ወጪን ያወጣል የተባለውን ክለብ ወጪ ለመቀነስ አንዱ መፍትሄ ሆኖ ቀርቧል።
የፕሪሚየር ሊጉን እና የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር የእግርኳስ ህጎች ለማክበርም ውሳኔው የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው የተባለው።
የዘንድሮውን የኤፍኤ ዋንጫ ከማንሳቱ ውጪ በፕሪሚየር ሊጉ ተፎካካሪነቱ እየቀነሰ የመጣው ማንቸስተር ዩናይትድ 1 ሺህ 150 ቋሚ ሰራተኞች አሉት።
በአንጻሩ ለአራት ተከታታይ አመት የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን የሆነው ማንቸስተር ሲቲ ተጫዋቾችና የቡድኑ አባላትን ጨምሮ 520 ሰራተኞች ነው ያሉት።
አርሰናል በ2023 ግንቦት ወር ላይ ይፋ ባደረገው መረጃ ተጫዋጮችን ጨምሮ አጠቃላይ ሰራተኞቹ 689 እንደነበር መግለጹ ይታወሳል።
ከዩናይትድ ተቀራራቢ የሰራተኛ ቁጥር ያለው ሊቨርፑል ሲሆን በሰኔ ወር 2023 1008 ሰራተኞች እንዳሉት ገልጾ ነበር፤ ከዚህ ውስጥ 701ዱ የአስተዳደርና የንግድ ሰራተኞች ሲሆኑ፥ 238ቱ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞችና ሌሎች የቡድን አባላት ናቸው።
ከሰው ሃይሉ አንጻር ያስመዘገበው ውጤት የሚመጣጣን አይደለም የተባለው ማንቸስተር ዩናይትድ፥ በሰር ጂም ራትክሊፍና በግሌዘር ቤተሰቦች ስምምነት ሰራተኞቹን እና ሌሎች ወጪዎቹን መቀነሱን እንደሚቀጥል ተገልጿል።