ተመድ ስለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ያወጣውን ሪፖርት ኤርትራ አልቀበለውም አለች
ተመድ ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት “በኤርትራ ያለው የስበዓዊ መብቶች ጥሰት ሁኔታ እየተባባሰ ነው” ማለቱ ይታወሳል
ኤርትራ “በሰብዓዊ መብቶች በኩል ያሉት ጉድለቶች”ን ለማሻሻል እየሰራሁ ነው ብላለች
ኤርትራ በሀገሪቱ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታን በማስመልከት በተመድ የቀረበው ሪፖርት እንደማትቀበለው አስታወቀች፡፡
በኤርትራ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታን ለመከታተል በተባበሩት መንግስታት የተሾሙት ሱዳናዊው ሞሃመድ አብደልሰላም ባቢከር (ዶ/ር) ሰሞኑን በኤርትራ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታን የተለመከተ ሪፖርት ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
አብደልሰላም ባቢከር (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት በኤርትራ ያለው የማያቋርጥ የ”ብሄራዊ አግልገሎት” መርሃ ግብር ነቅፈዋል፡፡
ይሁን እንጂ ኤርትራ አብደልሰላም ባቢከር (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ማዘኗን በተወካይዋ አማካኝነት ለምክርቤቱ ገልጻለች፡፡
በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የኤርትራ ተወካይ አምባሳደር ተስፋሚካኤል ገራህቱ ፤ ሞሃመድ አብደልሰላም ባቢከር (ዶ/ር) የኤርትራን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታን እንዲከታተሉ በአሜሪካ እና አጋሮቿ ከተሾሙበት የፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ እየተደረገ ያለው ነገር ኤርትራን ለማሳደድ ያለመ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
አምባሳደሩ “ የብሄራዊ አገልግሎት መርሃ-ግብር የኤርትራ መከላከያ ኃይል የጀርባ አጥንት ነው”ም ብለዋል፡፡
ካለምንም ስጋት በሰላም ለመኖር እንዲሁም የሀገርን ልዑላዊነት ለማስከበር ዋስትና የሚሰጥ መርሃ ግብር መሆኑም ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሩ እንዲህ ይበሉ እንጂ፤ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በኤርትራ ምድር ሲደረግ የቆየው አስገዳጅ “ብሄራዊ አገልግሎት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የሚፈጸምበት መሆኑ ዋነኛ መርሃ ግብር መሆኑ” ተመድ በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡
አሁን ላይ ያለው ሁኔታም ቢሆን “እጅጉን እየተባባሰ መሆኑ”ም ነው ሞሃመድ አብደልሰላም ባቢከር (ዶ/ር) ባቀረቡት ሪፖርት ያመላከቱት፡፡
ሌላው በሞሃመድ አብደልሰላም ባቢከር (ዶ/ር) አማካኝት በተመድ ስበዓዊ መብቶች ምክር ቤት የቀረበው ሪፖርት ያካተተው የኤርትራ ጉዳይም “በሀገሪቱ ምንም ዓይነት የፕሬስ ፣ የሃይማኖት፣ የመደራጀት እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት የለም” የሚል ነው፡፡
ዜጎች ኢ-ህጋዊ በሆነ መንገድ በየእስር ቤቶች ማጎርና ደብዛቸው እንዲጠፉ ማድረግ አሁን በኤርትራ ምድር እየተከናወነ ያለ ድርጊት እንደሆነም አብደልሰላም ባቢከር (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ አስረድቷል፡፡
በሀገሪቱ የሰብዓዊ መብቶች ለማስከበር ዋስትና የሚሰጥ ህግ የለም ሲሉም አክለዋል፡፡
የሰብዓዊ መብቶች ተቋም “ ኤርትራን የመገንባት ”አንዱ አካል ነው የሚሉት የኤርትራው ተወካይ ግን ፤ መንግስት “በሰብዓዊ መብቶች በኩል ያሉት ጉድለቶች ” ለማሻሻል እየሰራ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ተወካዩ፤ በትግራይ የኤርትራ ኃይሎች ፈጽመውታል ተብሎ በአብደልሰላም ባቢከር (ዶ/ር) የቀረበው የስበዓዊ መብቶች ጥሰት በተመለከተ ሲናገሩም “የተባለው ነገር ኤርትራ ሙሉ በሙሉ የማትቀበለው ነው” ሲሉ ተሰምተዋል፡፡
አክለውም ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት በኤርትራ ያለውን የስበዓዊ መብቶች ሁኔታ እንዲከታተሉ የተሸሙቱን አብደልሰላም ባቢከር (ዶ/ር) ስልጣን ለማራዘም የሚደረገው ጥረትና እቅድ እንዲቃወሙት ሲሉም ጠይቋል፤ የኤርትራው ተወካይ አምባሳደር ተስፋሚካኤል ገራህቱ ፡፡
የኤርትራ መንግስት በርካታ ወጣቶችን ለብሄራዊ አግልግሎት በሚል አስገድዶ ወደ ሳዋ (ማሰልጠኛ ማእከል) እንዲወርዱ ያደርጋል የሚሉ ክሶች በተለያዩ ጊዜያት ሲደመጡ ይስተዋላል፡፡
በዚህም በሺዋች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ወጣቶች፤ በግዳጅ ከሚከናወነው መርሃ ግብር ለመሸሽ በሚል ሀገራቸውን ጥለው ለስደት ሲዳረጉ መቆየታቸውና አሁንም እየተዳረጉ መሆናቸው የተመድ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
የ76 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኤርትራ ነጻነቷን ካወጀችበት የፈረንጆቹ 1991 ጀመሮ የሀገሪቱን በትረ ስልጣን በመጨበጥ ካለምንም ምርጫና ተቀናቃኝ ኤርትራን በመምራት ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡