የኤርትራው ፕሬዝዳንት “የምዕራባውያን ፖለሲ ዓለም አቀፍ ቀውስ እያስከተለ ነው” አሉ
ፕሬዝዳንቱ፤ ምዕራባውያን ታይዋንን ሽፋን በማድረግ ቻይናን ለመተንኮስ እየሄዱበት ያለው መንገድ አደገኛ ነው” ብለዋል
ኤርትራ ፤ በአከባቢውና በዓለም አቀፍ ደረጃ የራሷን ሚና እንደምትጫወትም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የምዕራባውያን ፖለሲዓለም አቀፍ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን ገለጹ።
ፕሬዝዳንቱ፣ የምዕራባውን ፖሊሲ ቀድሞውንም እንዳልተሳካ ገልጸዋል። ኢሳያስ አፈወርቂ ይህንን ያሉት “31ኛው የኤርትራ የነጻነት ቀን” በማስመለክት በአስመራ ስታዲየም ባደረጉት ንግግር ላይ ነው።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እ.ኤ.አ. በ 1991 ከቀዝቃዘው ጦርነት ማብቃትና የምስራቁ ካምፕ መፈረካከስ ወዲህ ያሉ ጊዜያት፤ የአሜሪካ እና የተወሰኑ ምዕራባውያንን የማይወክሉ ኃይሎች አስተሳሰቦች የበላይነት የተስተዋሉባቸው እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡
ምዕራባውያን ፖሊሲዎቻቸውንና ፍሎጎቶቻቸውን በተቀረው ዓለም ላይ ለመጫን ያደረጉት ሙከራ ስኬታማ ሊባል እንደማይችል ገልጸው፤ ይህ አካሄድ አሁንም ቢሆን ግን `` አደገኛ`` እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት የሳበው የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት፤ ምዕራባውያን የሩሲያን ጎረቤቶች እንደ መሳሪያ በመጠቀም ሞስኮን ለማምበረከክ ሲከተሉት የቆየ የተሳሳተ ፖሊሲ ውጤት መሆኑንም በአብነት አንስተዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
``የምዕራባውያን የተሳሳተ ፖሊሲ በዚህ አላበቃም`` የሚሉት ፕሬዝዳንቱ፤ አሜሪካና አጋሮቿ ታይዋንን እንደሽፋን በመጠቀም ቻይናን ለመተንኮስ እየሄዱበት ያለውን መንገድ “አደገኛ” መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የምዕራባውያን ፖለሲ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ቀውስ እያስከተለ እንደሆነ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ “ከቻይና ጋር ሊፈጠር የሚችለው ግጭት ከሩሲያው የባሰ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለኝ”ም ብለዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በተለያዩ አከባቢዎች የሚፈጠሩ ሁለንተናዊ ለውጦችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከቀጠናዊና አህጉራዊ ተቋማት ጋር አብሮ መስራት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑንም ነው ፕሬዝዳንቱ ያነሱት፡፡
ኤርትራ ከምታካሂደው የውስጥ ሀገራዊ ግንባታ በዘለለ፤ በአካባቢውና በዓለም አቀፍ ደረጃ የራሷን ሚና እንደምትጫወትም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አስታውቀዋል፡፡
እ.ኤ.አ ከ 1941 ጀምሮ የተጀመረው ``የኤርትራ ትግል`` በበርካታ ፈተናዎች ታጅቦና የተለያዩ ምዕራፎች ተሻግሮ አሁን ባለበት ከፍታ መድረሱን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ ረዥሙንና እልህ አስጨራሹን ጉዞ የፈጠራቸው እሴቶችን በመጠበቅና በማጎልበት አሁን ካለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ጋር መራመድ አስፈላጊ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የኤርትራ ትግል “የትውልዶች ቅብብል ነው” እንደሆነም ፕሬዝዳንቱ በሀገራቸው የነጻነት ቀን ላይ ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል፡፡