ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላት ግንኙነት በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገለጸች
የኢትዮጵያን እና የኤርትራን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚደርጉ የትብብር ማዕቀፎችን ለማበጀት እየተሰራ እንደሆነም ተገልጿል
መንግስት፤ ሱዳን የሰሜን ኢትዮጵያን ችግር እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅማ ``ወረራ ፈጽማለች`` ብሏል
ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላት አሁናዊ ግንኙነት በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የመስሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወር የሥራ ክንውን ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡ በሪፖርቱ አዲስ አበባ ከአስመራ ጋር ያላት ግንኙነት በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስቀምጠዋል፡፡
“ሕወሓት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙ እብደት ነው” ፕሬዝደንት ኢሳያስ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ የጋራ ጥቅሞቻቸውን መሰረት በማድረግ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሰረት የድንበር አካባቢና የሰዎች ዝውውርን የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች፣ የወደብ አጠቃቀም የንግድ ልውውጥ፣ የጉምሩክ፣ የኢሚግሬሽንና የመሳሰሉ የሁለቱን ሀገሮች ሕዝብ ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ የትብብር ማዕቀፎችን ለማበጀት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በውጭ የሚኖሩ የሁለቱ ሀገራት ዜጎች የተባበረ ድምጽ አዎንታዊ ሚና መጫወታቸውንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው፡፡
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ያላቸው የሕዝብ ለሕዝብ ቁርኝት ጠንካራ በመሆኑ በሁለቱ ሀገራት ያለው ሕዝብና በውጭ የሚገኙ የዲያስፖራ አባላት ተባብረውና ተደጋግፈው እንዲሰሩ ለማድረግ የበለጠ ስራ ሊሰራ ይገባልም ብለዋል አቶ ደመቀ፡፡
ሱዳን፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ችግር እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያን ድንበር ስለመውረሯም ተናግረዋል፡፡
“በሱዳን ወረራ ጉዳይ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዝምታን መምረጡ አሳዛኝ ነው”- አቶ ደመቀ መኮንን
አቶ ደመቀ፤ ሱዳን ድንበር ከመውረሯ በተጨማሪም የህወሓት መነሻ በመሆን ችግር መፍጠሯን ያነሱ ሲሆን ይህ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነት እጅግ አሻክሮታል ሲሉም ነው ለምክር ቤቱ የገለጹት፡፡
ሆኖም ሱዳን ምንም እንኳን ይህንን ብታደርግም፤ ኢትዮጵያ ግን የተፈጠረውን ችግሩ በሰላም መፍታት የተሻለ ነው ብላ እንደምታምን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡
ከሱዳን ጋር ያለውን ጉዳይ በተመለከተ ችግሩን ለመፍታት ስርዓት ያለ በመሆኑ መንግስት ሰላማዊ መፍትሄ ላይ ብቻ በማተኮር ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነም ነው አቶ ደመቀ ያስታወቁት፡፡
በአፍሪካ ቀንድ የሚከሰቱ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ኢትዮጵያ የበኩሏን ታደርጋለችም ብለዋል፡፡