ኤርትራ፤ “ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ስልጣናቸውን አላግባብ እየተጠቀሙበት ነው” ስትል ከሰሰች
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒሰትር "የዋና ዳይሬክተሩ ድርጊት ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ ሊያስወስድ የሚችል ነው" ብለዋል
ዶ/ር ቴድሮስ ከኤርትራ በኩል ለቀረበባቸው ክስ እስካሁን የሰጡት ምላሽ የለም
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶከተር ቴድሮስ አድሃኖም ስልጣናቸውን አላግባብ እየተጠቀሙበት ነው ስትል ኤርትራ ከሰሰች።
የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገጻቸው በሳሰፈሩት ጽሁፍ፤ “የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ሰልጣናቸውን አላግባብ እየተጠቀሙበት ነው” ብለዋል።
የማስታወቂያ ሚኒሰትሩ “ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ወያኔ ጓዶቻቸውን ከወንጀል ለመከላከል፤ በኤርትራ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የውሸት እና የክፋት ውንጀላዎችን መሰንዘር ቀጥሏል” ብለዋል።
የዋና ዳይሬክተሩ ማንነትን በተመለከተ ታሪክ ራሱ ስለሚናገር “ለማያቋርጥ የስኳር በሽታ ምላሽ መስጠት አያስፈልግም” ሲሉም ገልፀዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ በተገዳዳሚ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት ተጠያቂ ሲያደረጉ ይስተዋላል፡፡
በቅርቡ እንኳን፤ የዓለም የጤና ቀን ምክንያት በማድረግ በአሜሪካ በተሰናዳው መድረክ፤ ከትግራይ ጋር በተያያዘ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምለሽ፤ ሁለቱም መንግስታት ተጠያቂ ሲያደረጉ ተደምጠዋል
ዶ/ር ቴድሮስ በወቅቱ " እንደምታውቁት ትግራይ በኢትዮጵያና ኤርትራ ጦር ከበባ ውስጥ ከሆነች ከ500 ቀናት በላይ ተቆጥረዋል፤ ይህም በዘመናዊው የዓለም ታሪክ ረዥሙ ከበባ ነው" ነበር ያሉት።
ዋና ዳይሬክተሩ፤ ዓለም ለዩክሬን የሰጠውን ትኩረት ያክል " በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለትግራይ መስጠት አለበት" ሲሉ መጠየቃቸውም ይታወሳል።
ዶ/ር ቴድሮስ በትግራይ አለ ስለሚሉትን አሳሳቢ ጉዳይ በተለያዩ መድረኮች ሲናገሩ ቢደመጡም ግን፤ የኤርትራው ማስታወቅያ ሚኒስትር የማነ ገ/መስቀል የዋና ዳይሬክተሩ መግለጫዎችና ክሶች ትክክል አይደሉም ሲሉ አጣጥለዋል
ለዚህም "የዋና ዳይሬክተሩ ድርጊትና ባህሪ ከአንድ የተመድ ሰራተኛ የማይጠበቅና ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ ሊያስወስድ የሚችል ነው " ሲሉም አሳስበዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ ከኤርትራ በኩል ለቀረበላቸው ክስ እስካሁን የሰጡት ምላሽ የለም፡፡
ኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ግጭት ጉዳይ ዋና ዳይሬክተሩን ለቀድሞ ድርጅታቸው ህወሀት በመወገን የዲፕሎማሲ ድጋፍ አድረገዋል በማለት ሲከሳቸው እንደነበር ይታወቃል።
ዶ/ር ቴድሮስ በበኩላቸው “እኔ ለማንም አልወግንም ውግንናየ ለሰላም ነው” በማለት በወቅቱ ምለሽ መስጠታቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ዶ/ር ቴድሮስ ከተጣለባቸው ሃላፊነት ውጪ በሽብርተኝነት ለተፈረጀው ህወሓት ያደላ የፖለቲካ ውግንና አሳይተዋል የሚል ክስ እና የ‘ይመርመርልኝ’ ጥያቄ አቅርባ እንደነበረም ይታወሳል።
የዓለም ጤና ድርጅት ኮሚቴ፤ “ይህ እጅግ ውስብስብና ፖለቲካዊ መልክ ያለው እና ከኮሚቴው የአሰራር ሂደት ውጭ የሆነም ጉዳይ ነው” ማለቱ ይታወሳል።