የሰሜን ኢትዮጵያው ትግራይ ክልል "ስልታዊ" እገዳ ተጥሎበት ነበር-ዶ/ር ቴድሮስ
ዶ/ር ቴድሮስ የኢትዮጵያን ሁኔታ “በጣም አሳዛኝ” ነው ሲሉ ተናግሯል
ተመድ የሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ከገባ ከሶስት ሳምንታት በላይ ሆኖታል ብለዋል
በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኘው ትግራይ ክልል "ስልታዊ" እገዳ ተጥሎበት ነበር ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ተናገሩ፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በትግራይ ክልል ባለው የአቅርቦት እጥረት ምክንያት ሰዎች እየሞቱ እንደሆነ መግለጻቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
- “የእሱን ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች ወደ ጦርነት በገቡ ጊዜ ከእሱ ምን ልትጠብቁ ኖሯል”- ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ስለ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የተናገሩት
- ዶ/ር ቴድሮስ ከህወሓት ጋር ወግነዋል የሚለው ክስ “አውነት አይደለም” አሉ
ዶ/ር ቴድሮስ "አቅረቦት እና መድሃኒት ወደ ትግራይ መላክ አንችልም ምክንያቱም እገዳ ተጥለዋል፤ እገዳው ስልታዊ ነው" ብለዋል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ ባልተለመደ መልኩ በአደባባይ በተናገሩት ንግግር፤ የኢትዮጵያን ሁኔታ “በጣም አሳዛኝ” ሲሉ መግለጻቸውን ዘገባው ጠቅሷል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ወደ ክልሉ እርዳታ እንዳይገባና የአቅርቦት እጥረት እንዳይኖር ምክንያት የሆነውን አካል ከመናገር ግን ተቆጥበዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውንና “ሰው ሰራሽ” ነው ብሎ የሚጠራው የአቅረቦት ችግር እንዲቀረፍና እርዳታ ወደ ሰሜን እንዲላክ ለኢትዮጵያ መንግስት ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ተመድ ጥሪ ቢያቀርብም ግን የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ትግራይ እንዳይሄድ ያገደው እርዳታ እንደሌለ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ግጭት ጉዳይ ዋና ዳይሬክተሩን ለቀድሞ ድርጅታቸው ህወሀት በመወገን የዲፕሎማሲ ድጋፍ አድረገዋል በማለት ሲከሳቸው ቆይቷል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ በበኩላቸው “እኔ ለማንም አልወግንም ውግንናየ ለሰላም ነው” በማለት በወቅቱ ምለሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል የሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ከገባ ከሶስት ሳምንታት በላይ ተቆጥሯል፡፡
የተመድ መረጃ እንደሚያመክተው 364 የጭነት መኪኖች በአጎራባች ክልሎች እንደሚገኙና ከባለስልጣናት ፈቃድ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡
ወደ 80% የሚጠጋው አስፈላጊ መድሃኒት በትግራይ እንደማይገኝና አብዛኛዎቹ የጤና ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነም ነው የተገለጸው፡፡
በፌደራል መንግስት የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል አለመግባባት የተፈጠረው፤ ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ሲያስተዳድር የነበረው የገዥ ፓርቲ ግንባሮች በመዋሃድ ብልጽግና ፓርቲን ሲመሰርቱ ህወሓት የውህደቱ አካል አልሆንም ብሎ በማፈንገጡ ነው።
ህወሓት የፌደራል መንግስቱ ህገወጥ ነው ያለውን ምርጫ ማካሄዱም የአልመግባባቱ ጡዘት ውጤት ነበር።
በሁለቱ አካላት መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ወታራዊ ግጭት ያመራው፤ ጥቅምት 24፣2013ዓ.ም ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነበር፡፡
ክህደት ፈጽሟል ባለው ህወሓት ላይ “የህግ ማስከበር ዘመቻ” በማወጅ የትግራይ ዋና ከተማና ብዙ ቦታዎችን መያዝ የቻለው መንግስት ከ8 ወራት በኋላ ለትግራይ ህዝብ የጽሞና ግዜ ለመስጠት በማሰብ ከትግራይ ክልል ሰራዊቱን ማስወጣቱ ይታወሳል።
በክልሉ በነበረው ጦርነት ወቅት ዜጎች መፈናቃላቸውንና መገደላቸውን ኢሰመኮና ሌሎች አለምአቀፍ ተቋማት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
መንግስት ጦሩን ከክልሉ ማስወጣቱን ተከትሎ፣ ሕወሓት ወደ አማራ አፋር ክልል በመግባት ጥቃት ከፍቷል፡፡
አሁን ጦርነት ባለባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ህዝብ ለርሃብና ለሞት አደጋ የተዳረገ ሲሆን በ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ጦርነቱን በመሸሽ መፈናቀላቸውን የአማራ ክልል መንግስት መቅርቡ ገልጿል፡፡
መንግስት በኢትዮጵያ በሽብር የተፈረጀው ህወሓት ደቅኖታል ያለውን ሉአላዊነትን ችግር ውስጥ የሚያስገባ አደጋ ለመቀልበስ ባለፈው ሳምንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።
በአፍካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሰጉን ኦባሳንጆ፣ በኢትዮጵያ አንድ አመት ያስቆጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡