ቴድሮስ አድሃኖም በኢትዮጵያ ጉዳይ የግል አቋማቸውን እንዳያንጸባርቁ ኢትዮጵያ ጠየቀች
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ዋና ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ውግንናውን እየፈጸመ ነው ብሏል
ዋና ዳይሬክተሩ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታዎች እንዳይገቡ ከልክሏል ሲሉ ተናግረዋል
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በኢትዮጵያ ጉዳይ የግላቸውን አቋም እንዳያንጸባርቁ ኢትዮጵያ ጠየቀች፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ትናንትና በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ላሉ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ አግዷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
መንግስት በራሱ ዜጎች ላይ ምግብ፣ መድሃኒት እና ሌሎች የህይወት አድን ድጋፎችን እንዳያገኙ እገዳ ጥሏል ሲሉም ነበር ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡
ይህን ተከትሎ በመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ ጽህፈት ቤት በትዊተር ገጹ ፖለቲካዊ ውግንና አላቸው ያላቸው ዶ/ር ቴድሮስ ኢትዮጵያን ከተመለከቱ ጉዳዮች ራሳቸውን እንዲያርቁና ገለልተኛ እንዲሆኑ ጠይቋል፡፡
የተሰጣቸውን ዓለም አቀፋዊ ሚና ከመወጣት ይልቅ ከፖለቲካዊ እና ግለሰባዊ ፍላጎት የመነጨ ውግንናቸውን እያንጸባረቁ ነው ያለው ጽህፈት ቤቱ የተመድ ኤጀንሲዎች ስራም በዚሁ ምክንያት እየተስተጓጎለ ይገኛል ብሏል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያን ከተመለከቱ የትኞቹም ጉዳዮች ራሳቸውን እንዲያርቁም ነው፤ በአምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ የሚመራው በተመድ የኢትዮጵያ ተልዕኮ ጽህፈት ቤት የጠየቀው፡፡
ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት የጤና ተቋማት ሲወድሙ ምንም አላለም በሚል የዓለም ጤና ድርጅትን መውቀሷ ይታወሳል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ ከአሁን ቀደም በሰጡት መግለጫ በተፈጠረው ሁኔታ “ልቤ ተሰብሯል” በማለት ሁሉም አካላት ለሰላም እንዲሰሩና የሰላማዊ ዜጎችን ደህንነት እንዲጠብቁ ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡