የዓለም ጤና ድርጅት በዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ላይ የቀረበውን የምርመራ ጥያቄ አሁን ሊመለከት እንደማይችል አስታወቀ
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ይህ መባሉ አሁንም የድርጅቱን ወገንተኛነት የሚያሳይ ነው ብለዋል
ድርጅቱ ውሳኔውን ማዘግየቱን ኢትዮጵያ ተቃውማለች
ኢትዮጵያ በዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ላይ ያቀረበችው የ‘ይመርመርልኝ’ ጥያቄ ሊዘገይ ይችላል ተባለ፡፡
የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሁለት ሳምንት በፊት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከተጣለባቸው ሃላፊነት ውጪ በሽብርተኝነት ለተፈረጀው ህወሃት ያደላ የፖለቲካ ውግንና አሳይተዋል የሚል ክስ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
ሚኒስቴሩ ለድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ በላከው ደብዳቤም የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴድሮስ ትግራይ ክልልን በሚመለከት ሀሰተኛ መረጃዎችን አሰራጭተዋል ሲልም ከሷል፡፡
የድርጅቱ መርማሪ ቦርድ በዶ/ር ቴድሮስ ላይ ምርመራ እንዲያደርግ ደብዳቤ የደረሰው የዓለም ጤና ድርጅት መርማሪ ቦርድም በጉዳዩ ዙሪያ ዛሬ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ሊቀመንበር ፓትሪክ አሞጽ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት ምላሽ “የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ከኢትዮጵያ የቀረበለትን የምርመራ ጥያቄ ሊያዘገየው ይችላል” ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሊቀመንበሩ የዶ/ር ቴድሮስ ድርጅቱን ለሁለተኛ ጊዜ በዳይሬክተርነት ለመምራት እጩ ሆነው መቅረባቸውን በማስመልከት በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ ነው ይህን ያሉት፡፡
በመድረኩ ንግግራቸው “ይህ እጅግ ውስብስብና ፖለቲካዊ መልክ ያለው እና ከኮሚቴው የአሰራር ሂደት ውጭ የሆነም ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡
“በመሆኑም ጥያቄው ለጊዜው ቆይቶ ተገቢው አካል በተገቢው ጊዜ ምላሽ ቢሰጠው” የሚል አስተያየት እንዳላቸውም ነው ሊቀመንበሩ የተናገሩት፡፡
ከቦርዱ 34 አባላት አንደኞቹም አልተቃወሙትም፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ ለሮይተርስ ምላሽ የሰጡት የመንግስት ኮሙንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ድርጅቱ የቀረበለትን የምርመራ ጥያቄ ማዘግየቱን በሚመለከት በሰጡት ምለሽ የዓለም ጤና ድርጅት ገለልተኛ አይደለም ብለዋል፡፡
ዶ/ር ለገሰ አክለውም የኢትዮጵያ መንግስት አሁንም በዶክተተር ቴድሮስ አድሃኖም ወገንተኝነት ጉዳይ የቀረበለትን ምርመራ እንዲያደርግ በድጋሚ አሳስበዋል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፎች እንዳይገቡ ከልክሏል፣ ዜጎች በምግብ እና በመድሃኒት እጥረት እየሞቱ ነው ሲሉ ለብዙሃን መገናኛዎች መናገራቸው ይታወሳል፡፡