የዩክሬን ጉደይ በትግራይ ክልል ያለውን የጤና ቀውስ እንዲዘነጋ አድርጎታል- ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም
ዶ/ር ቴድሮስ “አዎ፣ እኔ የትግራይ ተወላጅ ነኝ፤ ይህ ችግር እኔን፣ ቤተሰቤንና ጓደኞቼን በግል ይነካል” ብለዋል
መንግስት “ዋና ዳይሬክተሩ ልክ እንደ ትግራይ በአማራና በአፋር የወደሙ የጤና ተቋማት ጉዳይ ሊያሳስባቸው ይገባል” ብሏል
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የዩክሬን ጉደይ በትግራይ ክልል ያለውን የጤና ቀውስ እንዲዘነጋ ማድረጉን አስታወቁ።
ዶ/ር ቴድሮስ፤ የዓለም ዓይኖች ዩክሬን ላይ መሆናቸው ነው የትግራይ ክልል የጤና ቀውስ የተረሳ ማለታቸውም ነው የፈረንሳዩ የዜና ወኪል /ኤ ኤፍ ፒ/ የዘገበው።
በየትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ “አሰቃቂ” ነው በማለት የገለጹት ዶ/ር ቴድሮስ፤ “6 ሚልየን የሚሆነው የክልሉ ህዝብ ለ500 ቀናት ያክል ከውጭው ዓለም ጋር እንዳይገናኝ ተደርጎ እንደተዘጋበት ነው” ብለዋል።
“ከታህሳስ ወር አጋማሽ ጀምሮ ምንም አይነት እርዳታ አልደረሰም” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ፤ በዓለም ጤና ድርጅት በተደረገ ግምገማ መሰረት የክልሉ ሶስት አራተኛ የጤና ተቋማት መውደማቸውም በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ባለፈው የካቲት ወር ለ300 ሺህ ሰዎች የሚበቃ 33.3 ሜትሪክ ቶን መድሃኒት እና የህክምና ቁሳቁሶች ወደ ትግራይ ማስገባት ቢቻልም፤ ይህ በክልሉ ላለው ችግር ምላሽ ለመስጠት ከሚያስፈልገው 2 ሺህ 200 ሜትሪክ ቶን እንጻር እጅግ ዝቅተኛ ነው ብለዋል።
እስካሁን ወደ ክልሉ የገባው አጠቃላይ የህክምና እርዳታ መጠን 117 ሜትሪክ ቶን (ከ1 በመቶ ያነሰ) ብቻ መሆኑንም ጭምር ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ 46 ሺህ የሚሆኑ በደማቸው ኤች.አይ.ቪ ያላቸው ሰዎች እንዲሁም የካንሰር፣ስኳር፣ቲቢ እና ተጓዳኝ በሽታ ታማሚዎች ህክምና ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ የለም ብለዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ በንግግራው አክለውም፤ “አዎ፣ እኔ የትግራይ ተወላጅ ነኝ፤ ይህ ችግር እኔን፣ ቤተሰቤን እና ጓደኞቼን በግል ይነካል” ነገር ግን እኔ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በመሆኔ ጤና አደጋ ላይ በወደቀበት ቦታ ሁሉ ጤናን የመጠበቅ እና የማስተዋወቅ ግዴታ አለብኝ ፤እናም በዓለም ላይ እጅግ የከፋ የጤና ቀውስ ያለው በትግራይ ነው” ሲሉም ተደምጧል።
ዶ/ር ቴድሮስ በዓፋር እና አማራ ክልል ያለው የሰብዓዊ ቀውስ ሁኔታ ከጊዜ ወደ እየተባባሰ መምጣቱንም ተናግረዋል።
በሁለቱም ክልሎች የመጠሊያ፣ ምግብ እና ህክምና ድጋፍ የሚሹ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መኖራቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ተፈናቃዮች ለመርዳት የተለያዩ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውንም አስታውቀዋል።
ሆኖም ግን በአማራ ክልል እና በአፋር ክልል በነበረው ጦርነት ስለወደሙ የጤና ተቋማት ከመናገር ተቆጥበዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት መግለጫቸው የዶ/ር ቴድሮስ መግለጫን በማስመለከት ምላሽ ሰጥተዋል።
በምላሻቸውም “ዋና ዳይሬክተሩ እንደ ትግራይ ሁሉ በህወሐት ምክንያት በአማራና በአፋር የወደሙትን የጤና ተቋማት ጉዳይ ሊያሳስባቸው ይገባል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ቀደም ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከተጣለባቸው ሃላፊነት ውጪ በሽብርተኝነት ለተፈረጀው ህወሃት ያደላ የፖለቲካ ውግንና አሳይተዋል በሚል፤ ለዓለም ጤና ድርጅት መርማሪ ቦርድ የ‘ይመርመርልኝ’ ጥያቄ እስከማቅረብ ደርሷል።
የድርጅቱ መርማሪ ቦርድ “ይህ እጅግ ውስብስብና ፖለቲካዊ መልክ ያለው እና ከኮሚቴው የአሰራር ሂደት ውጭ የሆነም ጉዳይ ነው” የሚል ምላሽ እንደሰጠም የሚታወስ ነው።