“የፌዴራል መንግስቱ እና ህወሓት ለድርድር ሊቀመጡ ከሚችሉበት የህግ እና የሞራል እኩሌታ ላይ አይደሉም”-የፌዴሬሽን ምክር ቤት
የፌዴራል መንግስቱ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመታደግ ካልቻለ እና መደራደርን ከመረጠ ወደ ፊት እጅግ አደገኛ ሁኔታ እንደሚገጥመውም አስታውቋል
“ከህወሓት ጋር ለድርድር መቀመጥ የፌዴራል መንግስቱን ህገ መንግስታዊ ኃላፊነት ማቅለል ነው”
“የፌዴራል መንግስቱ እና ህወሓት ለድርድር ሊቀመጡ ከሚችሉበት የህግ እና የሞራል እኩሌታ ላይ አይደሉም”-የፌዴሬሽን ምክር ቤት
ከህወሓት ጋር ለድርድር መቀመጥ የፌዴራል መንግስት በህገ መንግስቱ መሰረት የተሰጠውን ኃላፊነት ማቅለል ነው ሲል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሳሰበ፡፡
ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግስቱን ጣልቃገብነት በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡
ህወሓት በሃገሪቱ መከላከያ ሰራዊት እና በአጎራባቹ የአማራ ክልል ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ህግና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን እንዲያስከብር ለፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ የሚገባበትን ፍቃድ መስጠቱን ያስታወቀው ምክር ቤቱ አንዳንዶች ህግ የማስከበሩን ዘመቻ እንደ እርስበርስ ጦርነት በመቆጠር ለድርድር ጥሪ አቅርበዋል ብሏል፡፡
ሆኖም ከህወሓት ጋር ለድርድር መቀመጡ “የፌዴራል መንግስቱ ህገ መንግስቱንና የፌዴራል ስርዓቱን ለመጠበቅ የተሰጠውን ህገ መንግስታዊ ኃላፊነት ማቃለል” እንደሆነም ነው ያስታወቀው፡፡
በብረት የታገዘ አመጽ መቀሰቀስ፣ ከሌሎች ክልሎች ጋር ያሉ ችግሮችን ሰላማዊ ባልሆኑ መንገዶች ለመፍታት መሞከር እና የፌዴራሉን የሰላምና የጸጥታ ሁኔታ ማናጋት የፌዴራል መንግስቱ በክልሎች ጣልቃ እንዲገባ ሊጋበዝ የሚችልባቸው ህገ መንግስታዊ ምክንያች እንደሆኑም ምክር ቤቱ አብራርቷል፡፡
በትግራይ ክልል የነበረውን ሰራዊት ያጠቃውና የዘረፈው ህወሓትም እነዚህኑ የፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ እንዲገባ የሚጋበዝባቸውን ምክንያቶች ያሟላ ህገ ወጥ ድርጊት መፈጸሙንም ነው የገለጸው፡፡
ህገ መንግስታ ስርዓቱን አደጋ ላይ ከጣሉት ከእነዚህ አካላት ጋር መደራደሩ የፌዴራል መንግስቱን ኃላፊነት ማቃለል ይሆናል ሲልም በአጽንኦት ገልጿል፡፡
“ይህ እንዲሆን የሚፈቅደው ህገ መንግስት በራሱ በህወሓት ንቁ ተሳታፊነት ተዘጋጅቶ መጽደቁንም ማስታወሱ ይጠቅማል”ም ነው ምክር ቤቱ ያለው፡፡
በዚህ ምክንያት “ህወሓት የፌዴራል መንግስቱን ጣልቃ ገብነት ሊሞግት አልያም እንደራደር ሊል የሚችልበት አግባብ” እንደሌለም አስቀምጧል፡፡
በተጨማሪም የፌዴራል መንግስቱ ለድርድር ይቀመጥ ማለቱ “ለህወሓት ህጋዊና ሞራላዊ የእኩልነት ደረጃ”ን እንደመስጠት ተደርጎ እንደሚቆጠርም ነው ያስቀመጠው፡፡
ሊደራደሩ የሚችሉበት “ህጋዊም ሞራላዊም አግባብ የለም”ም ብሏል፡፡
የፌዴራል መንግስቱ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመታደግ እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡
ይህ ሳይሆን ቀርቶ የፌዴራል መንግስቱ ህገ መንግስታዊ ስልጣኑን ተጠቅሞ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመታደግ ካልቻለ እና መደራደርን ከመረጠ ወደ ፊት እጅግ አደገኛ ሁኔታ እንደሚገጥመው አሳስቧል፡፡
ይህ ማለት ሌሎች የፌዴሬሽኑ አካል የሆኑ የክልል መንግስታት የፌዴራሉን መንግስት ያለ ማንም ከልካይነት መገዳደር እንዲችሉ መፍቀድ ማለት እንደሆነም ነው ምክር ቤቱ “ሊታለፍ የሚችል” እንዳልሆነ በመጥቀስ ያሳሰበው፡፡