የኤርትራና ኬንያ መሪዎች የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በጋራ ለመስራት ተስማሙ
የኬንያና ኤርትራ ግንኙነት ባለፉት 30 አመታት ከፍ ዝቅ ሲል የቆየ መሆኑ ይታወቃል
አስመራና ናይሮቢ ያላቸውን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር ከስምምነት ደርሰዋል
በኤርትራ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ በትናንትናው እለት አስመራ የገቡት ኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በሁለት ቀናት ቆይታቸው ከኤርትራው አቻቻው ጋር ከተወያዩ በኋላ ሀገራቱ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ “የሁለትዮሽ ስምምነት መፈራረማቸው” የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የተደረሰው ስምምነት በሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊ እና የንግድ ትብብር ላይ ትኩርት ያደረጉ ናቸው ተብሏል፡፡
ሀገራቱ በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ትብብር በማድረግ የአፍሪካ ቀንድን ቀጠናዊ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውም ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ኢሳያስና የኬንያው አቻቻው ሩቶ ቀጠናዊ ውህደት በማረጋገጥ ረገድ በጋራ ለመስራት እና ለመምከር ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
በዚህም ሁለቱ መሪዎች በቀጠናው ያሉ ሀገራት ሰላምና መረጋጋትን ከማረጋገጥ አንጻር በቀጣናው ጠንካራ አመራር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር የሚለው መሪዎቹ የተወያዩበት ሌላው ጉዳይ ሲሆን በሁለቱን ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ለማጎልበት ተስማምተዋል፡፡
ግንኙነቱን እውን ለማድረግ የሁለቱም ሀገራት ዜጎች ወደ ኤርትራም ሆነ ናይሮቢ የሚያደርጉት እንቅስቀሴ ያለ ቪዛና ያልተገደበ ለማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት መሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
የንግድ ስምምነቱን በተመለከተም ሀገራቱ በየብስ፣ ባህር እና በአየር የሚደርጉት የንግድ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር መሪዎቹ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በኤርትራ ያደረጉትን ይፋዊ የስራ ገብኝት አገባደው ዛሬ ከሰአት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ አስታውቀዋል፡፡
የኬንያና ኤርትራ ግንኙነት ባለፉት 30 አመታት ከፍ ዝቅ ሲል የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡
እንደፈረንጆቹ ታህሳስ 2018 የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ናይሮቢን እንዲሁም በወቅቱ ኬንያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኡሁሩ ኬንያታ መጋቢት 2019 አስመራ የጎበኙባቸው ጊዜያት በአብነት ሊነሱ የሚችሉ ቢሆኑም፤ ጠንካራ ነው የሚባል የሁለትዮሽ ግንኙነት አላቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡
እናም የአሁኑ የፕሬዝዳንት ሩቶ ጉብኝት የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ሊያድሰው እንደሚችል ይታመናል፡፡