የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በኤርትራ እየሰለጠኑ ያሉ የሶማሊያ አየር ኃይል አባላትን ጎበኙ
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት የአራት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ኤርትራ ገብተዋል
ፕሬዝዳንት ሀሰን ከኤርትራው አቻቸው ኢሳያስ ጋር በቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራሉም ተብሏል
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ በኤርትራ ምጽዋ አቪዬሽን ኮሌጅ እየሰለጠኑ የሚገኙትን የሶማሊያ አየር ኃይል አባላን መጎብኘታቸው ተገለጸ፡፡
ፕሬዝዳንቱ የአራት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ሐሙስ እለት ኤርትራ መግባታቸው ይታወቃል፡፡
ሀሰን ሼክ መሃሙድ በኤርትራ ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በመገናኘት በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩም የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገ/መስቀል በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ አስታቀዋል፡፡
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረመስቀል ኤርትራ ያሉ የሶማሊያ አየር ኃይል አባላት በፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ እና ኢሳያስ አፈወርቂ ሲጎበኙ የሚያሳይ ፎቶ ይፋ አድርገዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ወደ ኤርትራ ጉዞ ሲያደርጉ በጥቂት ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡
የአሁኑ በፕሬዝዳንቱ የተመራው ከፍተኛ ልዑክ የሶማሊያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብስር ዑመር ጃማንም ጭምር ያካተተ ነው ተብሏል፡፡
ፕሬዝዳንተ ሀሰን ሼክ መሃሙድ ባለፈው ወርሃ ሐምሌ በኤርትራ ባደረጉት ጉብኝት ኤርትራ ያሰለጠነቻቸውን 5 ሺህ የሶማሊያ ወታደሮች መጎብኘታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ይሁን እንጅ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ (ፋርማጆ) ዘመን ወደ ኤርትራ እንደሄዱ የሚነገርላቸው ሰልጣኞች ሁኔታ ግልጽ ስላልነበር ሶማሊያውያን ወላጆች በልጆቻቸው ምክንያት ለከፍተኛ ጭንቀት ተዳርገው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከጉብኝታቸው መልስ የተወሰኑ ወላጆች ጋር ተገናኝተው ስለ ልጆቻቸው ህልውና ሲናገሩና ሲያጽናኑ የታዩበት አጋጣሚም ነበር ወቅቱ፡፡
ፕሬዝዳንቱ የሚያለቅሱትን ወላጅ ሲያጽናኑ “ አይዞን፤ የደስታ ቀናት እየመጡ ነው” ሲሉም ነበር ፕሬዝዳንቱ ወላጆችን ሲያናገሩ በተለቀቀው ቪዲዮ የተደመጡት፡፡
ፕሬዝዳንቱ በመስከረም ወር ለተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ወደ አሜሪካ ተጉዞው ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር በነበራቸው ቆይታ በኤርትራ የሚገኙትን ወታደሮቻቸው ለመመለስ የአሜሪካን ድጋፍ እንደጠየቁ በወቅቱ አነጋጋሪ የነበረ ጉዳይ ነው፡፡