ፕሬዝዳንት ሩቶ በኤርትራው አቻቸው ግብዣ አስመራ ቢገቡም ስለጉብኝቱ አላማ የተባለ ነገር የለም
የኬንያው አዲስ ፕሬዝዳንት ዊሊም ሩቶ ለይፋዊ ስራ ጉብኝት አስመራ መግባታቸው የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በትናንትናው እለት በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ እንደገለጹት ከሆነ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ኤርትራን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ሩቶ በሀገሪቱ የሁለት ቀናት ቆይታ ይኖራቸዋል፡፡
ሚኒስትሩ ይህን ይበሉ እንጅ የጉብኝቱ ዋና ዓላማ ምን እንደሆነ በተመለከተ ያሉት ነገር የለም፡፡
ባሳለፍነው ወርሃ ታህሳስ 3 ቀን 2022 ኤርትራው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዑስማን ሳልሕ ወደ ኬንያ አቅንተው ከፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር መገናኘታቸው አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጅ ሩቶ ወደ አስመራ ሊያቀኑ እንደሚችሉ በወቅቱ የተሰጠ ምንም ፍንጭ አልነበረም፡፡
የአሁኑ የሩቶ የአስመራ ጉብኝት በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ግብዣ መሰረት የተደረገ መሆኑም ነው ሚኒስትሩ የማነ ገብረመስቀል የገለጹት፡፡
እንደፈረንጆቹ ታህሳስ 2018 የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ናይሮቢን እንዲሁም በወቅቱ ኬንያ ፕሬዝዳንት ነበሩት ኡሁሩ ኬንያታ መጋቢት 2019 አስመራ ጎብኝተው ነበር።
የአሁኑ የፕሬዝዳንት ሩቶ ጉብኝት የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ሊያድሰው ይችላል ተብሎ ይታመናል፡፡
አስመራ የሚገኙት ዊሊያም ሩቶ “ኬንያ ከኤርትራ ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት ከፍ አድርጋ ትመለከታለች እናም ይህንን ትብብር ለሁለቱ ሀገራት ቀጣናዊ መረጋጋት እና ብልጽግና ለማስፋት ትፈልጋለች” ሲሉ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር ያለቸውን ፍላጎት በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ገልጸዋል፡፡
በተያየዘ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት በቀጣናው ስላም ለማምጣት እንደሚሰሩ ተናግረው ነበር።
ኘሬዝደንቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በግሬት ሌክስ ሪጂን ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የቀድሞውን ኘሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታን መወከላቸውን አስታውቀው ነበር።
ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል የዘላቂ የግጭት ማቆም ስምምነት በደቡብ አፍሪካ እንዲደረስ አደራድረዋል።
በተጨማሪም ደም አፋሳሹ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ በማድረግ በኩል ትልቅ ሚና ስትጫወት ቆየችው ኬንያ፤ ባሳለፍነው ወርሃ ህዳር የፌዴራል መንግስትና ህወሓት ወታደራዊ አዛዦች አስተናግዳ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
በድርድሩ ወቅት ሁለቱ አካላት የውጭ ኃይሎች ከኢትዮጵያ ይውጡ የሚል ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የውጭ ኃይሎች የተባሉት ህወሓት የኤርትራ ጦርን እንደሆነ ገልጿል።
ፕሬዝደንት ዊሊያም ከፕሬዝደንት ኢሳያስ ጋር በዚህ ጉዳይ ስለመነጋገራቸው ያሉት ነገር የለም።
ይሁን እንጅ ኬንያታ ከፕሬቶሪያ በመቀጠል በናይሮቢ በነበረው የፊርማ ስነ-ስርአት ኤርትራን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት አስተያየት መስጠት እንደማይፈለጉ ተናገሩበት አጋጣሚም አይዘነጋም፡፡