ኢትዮጵያ ለኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ የኤሌክትሪክ ሀይል መሸጥ ልትጀምር ነው
በሰመራና ሚሌ ከተሞች የሀይል ማከፋፈያ ግንባታ በ1 ዓመት ውስጥ ለመገንባት ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቷል
ኢትዮጵያ ለጅቡቲ እየተሸጠ ያለውን ሀይል በእጥፍ ለማሳደግ አዲስ የሀይል ስምምነት ፈጸመች
ኢትዮጵያ ለኤርትራ ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ የኤሌክትሪክ ሀይል መሸጥ ልትጀምር ነው።
የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ የሚንስትሮች ጉባኤ በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን የሁለቱ ሀገራት የኤሌክትሪክ ሀይል ሀላፊዎች አዲስ የሀይል ሽያጭ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን ኢትዮጵያ ለአዳዲስ የጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ሀይል መሸጥ የሚያስችላትን የአዋጭነት ጥናት በማካሄድ ላይ እንደምትገኝ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የኮርፖሬት ፕላኒንግ ስራ አስፈጻሚ አቶ አንዱዓለም ሲአ ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት ለኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ የኤሌክትሪክ ሀይል ለመሸጥ መታቀዱን ገልጸዋል።
እንደ ስራ አስፈጻሚው ገለጻ ኢትዮጵያ ለሁሉም የጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ሀይል ለመሸጥ አቅዳለች።
ለሶስቱ የጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ሀይል ለመሸጥ የአዋጭነት ጥናት በመካሄድ ላይ መሆኑን የነገሩን አቶ አንዱዓለም ይህ ጥናት በቅርቡ ከተጠናቀቀ በኋላ በሚቀጥለው ዓመት የሀይል ሽያጭ ስምምነት ከገዢ ሀገራቱ ጋር ስምምነት እንደሚፈጸም አክለዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ለሱዳን እና ጅቡቲ የኤሌክትሪክ ሀይል በመሸጥ ላይ ስትሆን ለኬንያ ደግሞ የሀይል ሽያጭ ስምምነቱ እና ግንባታው መጠናቀቁን ተቋሙ ከዚህ በፊት መናገሩ ይታወሳል።
ይህ በዚህ እንዳለ ለጅቡቲ እየተሸጠ ያለውን ሀይል በእጥፍ ማሳደግ የሚያስችል አዲስ ስምምነት በአዲስ አበባ ተፈጽሟል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ለጅቡቲ 600 ጊጋ ዋት ሰዓት ሀይል በመሸጥ ላይ ስትሆን የሀይል ሽያጩን በእጥፍ ለማሳደግ ተስማምታለች።
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ አሁን ካለው የሀይል ማስተላለፊያ ተጨማሪ መስመር ለመገንባትም ከጅቡቲ መንግስት ጋር አዲስ ስምምነት መፈጸሟን አቶ አንዱዓለም ተናግረዋል።
292 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው አዲስ ተጨማሪ የሀይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ኢትዮጵያ 102 ኪሎ ሜትር ጅቡቲ ደግሞ 190 ኪሎ ሜትር እንደሚገነቡ በስምምነቱ ላይ ተገልጿል።
የዚህ አዲስ የሀይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ የአዋጭነት ጥናት በፈረንሳዩ ትሬክ ቴብል በተሰኘ ኩባንያ ተጠንቶ መጠናቀቁን ተከትሎ የግንባታ ጨረታ መውጣቱንም አቶ አንዱዓለም ገልጸዋል።
የሀይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ወጪ ከዓለም ባንክ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ብድር እንደሚሸፈን ሰምተናል።
ለጅቡቲ ለሚሸጠው የኤሌክትሪክ ሀይል ሲባልም በኢትዮጵያ ውስጥ ሰመራ እና ሚሌ ከተሞች እንዲሁም በጅቡቲ በኩል ደግሞ ናጋድ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ የሀይል ማከፋፈያ ማስፋፊያ እና አዲስ ግንባታ እንደሚካሄድ አቶ አንዷለም ገልጸዋል።
ይህ አዲስ ግንባታ በአንድ ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ያሉን አቶ አንዱዓለም ለሱዳንም አሁን እየተሸጠ ካለው ሀይል ባለፈ ተጨማሪ ሀይል ለመሸጥ መታቀዱንም ከሀላፊው ሰምተናል።
ኢትዮጵያ በሀምሌ እና ነሀሴ ሁለት ወራት ለሱዳንና ለጅቡቲ ከተሸጠ ኤሌክትሪክ ኃይል ከ13 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ሽያጭ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወሳል።