ኤርትራ በአሜሪካ የተጣለውን የቪዛ እገዳ “ለቀጠናው የማይበጅ” ስትል ተቃወመች
አሜሪካ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ እንዲሁም በሕወሓት ባለስልጣናትና የጸጥታ ኃይሎች ላይ የቪዛ እገዳ መጣሏ ይታወሳል
ለዚህ ሁሉ ቀውስ ተጠያቂው ህወሓት እንደሆነ ነው ኤርትራ የገለጸችው
አሜሪካ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ከተከሰተው ቀውስ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ የቀድሞ እና የአሁን ባለስልጣናትና የጸጥታ ኃይሎች ላይ (ህወሓትን ጨምሮ) የቪዛ እገዳ ከቀናት በፊት መጣሏ የሚታወስ ነው፡፡
ኤርትራ የተጣለውን እገዳ “ምንም ማረጋገጫ የሌለው” ያልተገባ ውሳኔ ነው ስትል ተቃውሞዋን ገልፃለች፡፡
ማእቀቡ ሀገሪቱ “30ኛ የነጻነት በዓሏን” በምታከብርበት ዋዜማ መሆኑ እጅጉን እንዳስቆጣትም ኤርትራ አስታውቃለች፡፡
የተጣለው እገዳ “ለቀጠናው ሰላምና ፀጥታ እንዲሁም ህጋዊነት የሚበጅ አይደለም” ነው ያለችው ኤርትራ በውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር መስርያ ቤቷ በኩል ባወጣችው መግለጫ።
ሚኒሰቴሩ "በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የተፈጠረው ቀውስ አሁን ላይ የፈረሰው ሕወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የወሰደውን ወታደራዊ እርምጃ ተከትሎ የተፈጠረ ነው" ሲል ከሷል፡፡
"የህወሓት ወታደራዊ እቅድ ኢትዮጵያን ብቻ ያለመ አልነበረም ፤ ኤርትራንም ጭምር እንጂ" በማለትም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡ ግጭቱ መጀመሩን ተከትሎ የህወሓት ኃይሎች ወደ ኤርትራ ሮኬቶችን ማስወንጨፋቸውን ሚኒስቴሩ በአብነት አንስቷል፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሕወሓት የሚመሩ ኃይሎች በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን በመግለጽ ፣ ነበር ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አሕመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ያወጁት፡፡
አሁን አሸባሪ ተብሎ በሀገሪቱ ፓርላማ የተፈረጀው የሕወሓት መሪዎች ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የተወሰደው የማጥቃት እርምጃ "ቅድመ-መከላከል" ነው በማለት ሲሞግቱ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
የአሜሪካ መንግስት የኤርትራ ኃይሎች በትግራይ ወንጀል ፈፅመዋል የሚሉ ክሶች ሲያቀርብና እንዲወጡ ሲወተውት ቢቆይም፤ ኤርትራ ተፈፀሙ የተባሉ ወንጀሎች እንደማይመለከቷት እና እንደማትቀበል ስትገልጽ ቆይታለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አሕመድ እና የኤርትራ ባለስልጣናት የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ ምድር ለቆ እንዲወጣ ተስማምተናል ቢሉም፤ እስካሁን የመውጣት ዝንባሌዎች እንደሌሉ የተለያዩ ዘገባዎች እየገለፁ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ መቋጫ ያገኛል የተባለው ወታደራዊ እርምጃም አሁን ድረስ እየቀጠለ መሆኑን እና ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊ ቀውስ ማስከተሉንም እንዲሁ፡፡