እስካሁን 18 የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች የሚገኙባት ኤርትራ ቫይረሱን ለመቆጣጠር እርምጃዋን አጠናክራለች
እስካሁን 18 የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች የሚገኙባት ኤርትራ ቫይረሱን ለመቆጣጠር እርምጃዋን አጠናክራለች
የኤርትራ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል ከፍተኛ ታስክ ፎርስ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የሀገሪቱ ዜጎች ለቀጣይ 21 ቀናት ከቤታቸው እንዳይወጡ እገዳ አስቀምጧል፡፡
የሀገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው እንዳሉት እገዳው እጅግ አስፈላጊ በሆኑ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን እና የጸጥታ አካላትን አያካትትም፡፡
ከምግብ እና መጠጥ፣ ከፋርማሲ እና ከባንክ ተቋማት ውጭ የሚገኙ ሁሉም የንግድ ተቋማት እንዲዘጉም ተወስኗል፡፡
በግብርናና የከብቶች እርባታ መስክ የተሰማሩ የገጠር ነዋሪዎች ግን ተግባራቸውን ከማከናወን አልተከለከሉም፡፡
የመንግስት ተቋማት ከቫይረሱ ስጋት ጋር በተያያዘ የእለት ከእለት መደበኛ ስራቸውን እንዲያቆሙም ነው የተወሰነው፡፡
ለምግብ እና መሰል አስፈላጊ ሸቀጦች ሸመታ ከአንድ ቤት ከ ሁለት ሰው በላይ መውጣት አይችልም፡፡
አዲስ የተደነገገው አዋጅ በዜጎች የእለት ከእለት ኑሮ ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ከፍተኛ እንደሆነ መንግስት ይገነዘባል ያሉት አቶ የማነ ገብረ መስቀል፣ ይሁንና ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ውሳኔውን ከመወሰን ውጭ ምንም አማራጭ የለውም ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ የመተባበር ባህሉን ይበልጥ በማጠናከር ይሄን አስቸጋሪ ጊዜ በጋራ ሊወጣ እንደሚገባም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በሀገሪቱ እስካሁን 18 የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ተገኝተዋል፡፡ ከቫይረሱ ታማሚዎች አብዛኛው ከውጭ ወደ ሀገሪቱ የገቡ ኤርትራውያን ናቸው፡፡ በትናንትናው እለት ለይቶ ማቆያ ውስጥ ከነበሩ ሰዎች መካከል 3 ግለሰቦች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከነርሱም አንዷ ከእናቷ የተላለፈባት የ 13 ዓመት ታዳጊ ናት፡፡ ሀገሪቱ ጠንካራ ውሳኔ እንድታስተላልፍ ምክንያት የሆናትም የታዳጊዋን በቫይረሱ መያዝ ተከትሎ በሀገሪቱ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፉ እድል ሊሰፋ ይችላል የሚል ስጋት ነው፡፡
ውሳኔውን ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም ግለሰብ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድበትም መንግስት ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
የሀገሪቱ መንግስት ኮሮናን ለመከላከል እያደረገ በሚገኘው የገቢ ማሰባሰብ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከህዝቡ አንድ ሚሊዮን ዶላር ማሰባሰቡንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡