ኤርትራ በአሜሪካ የተጣለባትን የጉዞ እገዳ ተቀባይነት የሌለው በማለት ተቃወመች
የናይጄሪያ፣ የኤርትራ፣ የታንዛኒያ፣ የሱዳን፣ የኪርጊስታን እና የማይናማር ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያግድ የተለያየ አይነት የጉዞ እገዳ ከትናንት በስቲያ በትራምፕ አስተዳደር ተጥሎባቸዋል፡፡
ሀገራቱ እገዳው የተጣለባቸው የአሜሪካን የደህንነትና የመረጃ ልውውጥ መርህ ደረጃ አያሟሉም በሚል ምክኒያት መሆኑን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡
እኤአ በ2018 አሜሪካ ለናይጄሪያ እገዳው የተጣለባቸው ሌሎች አምስቱ ሀገራት በድምር የተሰጣቸውን 2 እጥፍ ያክል የኢሚግሬሽን (የዜግነት) ቪዛ ለናይጄሪያውያን ሰጥታለች፡፡ በአመቱ 8018 ናይጄሪያውያን እድሉን አጊኝተዋል፡፡
የአሁኑን የአሜሪካ ውሳኔ በተመለከተ መግለጫ ያወጡት የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ሀገራቸው ከአሜሪካ ጋር ያላትን ውጤታማ ግንኙነት፣ በተለይም ከአለም ደህንነት አንጻር ያላትን ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡
ናይጄሪያ ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ እንዳቋቋመችም አስታውቃለች፡፡
በአፍሪካ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ናይጄሪያ ዜጎቻቸው ቋሚ የመኖሪያ ቪዛ ከተነፈጉት ሀገራት ትልቋ ነች፡፡ ኤርትራ፣ኪርጊስታን እና ማይናማርም ተመሳሳይ እገዳ ተጥሎባቸዋል፡፡ ሱዳንና ታንዛኒያ ደግሞ ከዚህ በኋላ የዲቪ ሎተሪ የተነፈጉ ሀገራት ናቸው፡፡
እገዳውን የተቃወሙት የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ እርምጃው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የሚጎዳ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው ነው ብለዋል፡፡ ይህ የአሜሪካ ድርጊት ተቀባይነት የለውም ያሉት ሚኒስትሩ ይሁንና ሀገሪቱ የአሜሪካ አምባሳደሯን እንደማትመልስ ገልጸዋል፡፡
ምንጭ፡- ሮይተርስ