
አዲሱ ምርት የአሜሪካው አይፎን ኩባያን ለመፎካከር ተብሎ የተሰራ እንደሆነ ተገልጿል
ሶስት ቦታ የሚተጣጠፈው አዲሱ የሁዋዌ ስልክ
በዓለማችን ካሉ ቀዳሚ የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ሁዋዌ አዲስ ስልክ ለገበያ አቅርቧል፡፡
መሰረቱን ቻይና ያደረገው ይህ ኩባንያ ሶስት ቦታ መተጣጠፍ የሚችል ቅንጡ ስልክ በማሌዢያ ኩዋላላምፑር በተካሄደ የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሽያጭ ቀርቧል፡፡
በሶስት ሺህ ዩሮ ለሽያጭ ቀርቧል የተባለው ይህ አዲስ ምርት የ10 ኢንች ስክሪን ስፋትም አለው ተብሏል፡፡
አዲሱ የህዋዌ ምርት እንደ ስልክም እንደ ፓድም ሆኖ ያገለግላል የተባለ ሲሆን መተጣጠፉ ደግሞ በቀላሉ ለመያዝ እና ለመጠቀም እንዲያገለግል ሆኖ መሰራቱ ተገልጿል፡፡
ህዋዌ ኩባንያ በበርካታ የምዕራባዊን ሀገራት ለቻይና መንግስት የተጠቃሚዎችን መረጃ ይሰጣል በሚል ማዕቀብ ተጥሎበታል፡፡
ኩባንያው እንደሚለው ከሆነ አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባዊን ሀገራት ማዕቀብ የጣሉት የደህንነት ስጋት በመሆኑ ሳይሆን የቴክኖሎጂ የበላይነቱን ለማስቆም በሚል ነው፡፡
ይህ መሆኑ ደግሞ የዓለም ቴክኖሎጂ መሪ የሖኑት እንደ ጎግል እና መሰል ኩባንያ ምርቶችን እንዳይጠቀም እና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆን እንቅፋት ፈጥሮበታል፡፡
ይሁንና ኩባንያው ማዕቀቦችን ሁሉ ተቋቁሞ ቀዳሚ የቴክኖሎጂ ኩባንያ መሆን መቻሉ ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ሁዋዌ በቻይና 49 በመቶ የገበያ ድርሻን ሲያዝ በዓለም ደግሞ የ23 በመቶ የገበያ ድርሻ እንዳለው በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡