ፕሬዝደንት ኢሳያስ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሱዳን ዲፕሎማትን አነጋገሩ
ፕሬዝዳንቱ ከአልቡርሃን ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዳፋላህ አልሃጅ ጋር ሲመክሩ፥ የውጭ ጣልቃገብነት የሱዳንን ውጥረት ያባብሰዋል ብለዋል
በሱዳን ጦርነት ዙሪያ ጎረቤት ሀገራትና ቀጠናዊ ድርጅቶች በሚኖራቸው ሚና ዙሪያም ሃሳባቸውን ሰጥተዋል
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሱዳን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሱዳን ዲፕሎማትን ተቀብለው አነጋግረዋል።
የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት መሪው ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን የላኩላቸውን መልዕክትም መቀበላቸውን የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የጀነራሉን መልዕክት ያደረሱት ልዩ መልዕክተኛቸው አምባሳደር ዳፋላህ አልሃጅ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከአምባሳደሩ ጋር ሱዳን አሁን ባለችበት ሁኔታ፣ በጎረቤት ሀገራት እና እንደ ኢጋድ ያሉ ቀጠናዊ ድርጅቶች ሚና ዙሪያ መክረዋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ።
የሱዳን ወቅታዊ ችግር በራሳቸው በሱዳናውያን ብቻ መፈታት እንዳለበት ያሳሰቡት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፥ ተፋላሚዎቹ ወገኖች በፍጥነት ተኩስ እንዲያቆሙ መጠየቃቸውንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
የውጭ ጣልቃገብነት የሱዳንን ወቅታዊ ችግር ይበልጥ ሊያወሳስበው እንደሚችልም ለአምባሳደር ዳፋላህ ነግረዋቸዋል።
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ሚናም ድጋፍ ከመስጠትና ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ያለፈ መሆን እንደማይገባው ፕሬዝዳንቱ ማሳሰባቸውን የማነ ገብረመስቀል አመላክተዋል።
አስመራ ለፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ መሪ ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ ድጋፍ እየሰጠች ነው የሚሉና ተያያዥ ዜናዎች ሀሰተኛ መሆናቸውንና የተለመደው የኤርትራን ስም የማጠልሸት ዘመቻ አካል አድርገው እንደጠቀሱትም ነው የማስታወቂያ ሚኒስትሩ በትዊተር መልዕክታቸው ያሰፈሩት።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከ12 ቀናት በፊት ከሀገራቸው የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ የሱዳን ግጭት አንገብጋቢ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆም ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።
“የሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች የለውጥ ሂደቱን በብቸኝነት የሙጥኝ የሚሉበት ጊዜ አይደለም፤ ይህ ጊዜ የፖለቲካ ንትርክ ወይም የስልጣን ሽኩቻ አይደለም" ሲሉ ነገሮችን በእርጋታ ማየት እንደሚገባ መግለጽቸውም አይዘነጋም።
በሱዳን ከፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በተጨማሪ የተጠቁ ቡድኖች መበራከት ችግር መፍጠሩን በማንሳትም የተዛቡ ያሏቸውን ድርጊቶች የማረም ስራው ለሱዳን ህዝብ ሊተውለት እንደሚገባ አሳስበዋል።