የኤርትራ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ጉብኝት መልዕክት ምንድን ነው?
ሰሞነኛው የኤርትራ የጦር አዛዦች ጉብኝት ለሰላም ስምምነቱ ገቢራዊ በጎ ሚና እንዳለው ተንታኞች ይናገራሉ
ከሰሜኑ ጦርነት ማብቃት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የአዛዦቹ ጉብኝት ለመቀራረብና አመኔታን ለማግኘት ያስችላል ተብሏል
የኤርትራ ከፍተኛ የጦር ልዑክ ካለፈው እሁድ ጀምሮ እስከ ትናንት ምሽት ድረስ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርግ ቆይቷል።
በብሄራዊ የደህንነት ኤጀንሲ ኃላፊ ብርጋዴር ጀነራል አብርሃ ካሳ የተመራው ልዑክ የተለያዩ የደህንነትና የመንግስት ተቋማትን የጎበኘ ሲሆን፤ ጉብኝቱ "የሁለቱ ሀገራት መልካም ግንኙነት አካልና ሀገራቱ የውትድርና ትብብራቸውን ለማጠናከር" ያለመ መሆኑን የኤርትራ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
አዲሱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በአዲስ አበባ ከመከረና እንደ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጄንሲ (ኢንሳ) ያሉ ተቋማትን በጎበኘ በማግስቱ የተጀመረው የኤርትራ ጦር አመራች ጉብኝት፤ ከህዳሴ ግድብ እስከ አየር ኃይልና ሌሎችም ተቋማትን አካሏል።
ከፍተኛ የጦር አዛዦች ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያን ሲጎበኙ (በይፋ) የመጀመሪያ ነው። በኢትዮጵያ በኩል የጉብኝቱ ዓላማ በይፋ ባይነገርም፤ ኤርትራ በጦርነቱ የነበራት ሚና፣ በሰላም ስምምነቱና በሀገራቱ ግንኙነት ላይ አዎንታዊ አንደምታ እንደሚኖረው ተንታኞች ለአል ዐይን ተናግረዋል።
- “የኤርትራ ሰራዊት ከኢትዮጵያ መውጣት ለዘላቂ ሰላም ቁልፍ ሚና አለው”- አሜሪካ
- የኤርትራው ፕሬዝዳንት “የምዕራባውያን ፖለሲ ዓለም አቀፍ ቀውስ እያስከተለ ነው” አሉ
ከከል አይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት ባለሞያዎች ሰሞነኛ ጉብኝቱን የሀገራቱን አጋርነትን፣ ዋጋ መስጠት፤ ለሰላም ስምምነቱ ገቢራዊነት ስጋትን ለመቀነስ በበጎ ተመልክተውታል።
በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት አበበ ይርጋ፤ የኤርትራን የጦርነቱን ሚናና የሰላም ስምምነቱን ጠቅሰው ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ መተማመኛ እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
"ህውሓት ተነስቶ እንዲተነኩሳት አትፈልግም፤ ሉዓላዊነቷ እንዲደፈር አትፈልግም፤ ለተጨማሪ ጥቃት ላለመዳረግ ዋስትና ትፈልጋለች፤ ያለውን ሁኔታም ማወቅ ያስፈልጋታል” ሲሉም ተናግረዋል።
“የጎበኟቸው ቁልፍ የደህንነት ቦታዎችን ነው፤ ይህም የኤርትራ መንግስትን ምን ያህል እንደምናቀርባቸው፤ እምነት እንዲያሳድሩብን እንደፈለግን ማሳያ ነው" ብለዋል።
የህግና የፖለቲካ ተንታኝ ሆኑት ቶማስ ታደሰ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርም ከቀናት ቀደም ብሎ ተመሳሳይ ጉብኝት ማድረጉን በመጥቀስ፤ "የኤርትራ ልዑክ ጉብኝት በዋናነት ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው" ሲሉ ለአል ዐይን ተናግረዋል።
“ከጦርነት በኋላ ውስብስብ ፖለቲካና የአሰላለፍ ለውጥ አይቀሬ ነው” የሚሉት ተንታኙ፤ ጉብኝቱም የዚህ አካል ሳይሆን አይቀርም ሲሉም ገልጸዋል።
"[ጉብኝቱ] በምስል እንዲታይ ተፈልጓል፤ የህውሓትና የትግራይ ጊዜያዊ አመራሮች ላደረጓቸው ጉብኝቶች፣ ውይይቶች ምላሽ የሚሆን ነገር ከኤርትራ መስጠት እንደታሰበ ያሳያል" በማለት እስካሁን ይፋዊ መግለጫ አለመሰጠቱንና ጉብኙቱ ለበርካታ ቀናት በተለያዩ ተቋማት መዝለቁን በመጥቀስ ተናግረዋል።
ለኤርትራ መተማመኛ መስጠትን በተመለከተ መተማመኛው ለሰላም ሚና ቢኖረውም ኢትዮጵያ ከቃል ያለፈ እርምጃ ያስፈልጋታል ባይ ናቸው።
"መሬት ላይ ሲወርድ ይህ መተማመኛ በምን አግባብ ነው የሚሰጠው? ምክንያቱም የኤርትራ መንግስት ከበፊት ጀምሮ ህውሓትን የሚከሰው 'የጦርነት ፍላጎት ያለው፣ መንግት እንዲረጋጋ የማይፈልግ፣ ከምዕራባዊያን ኃይሎች ጋር አብሮ ከኤርትራ በተቃራኒ የሚሰራ' እያለ ነው። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች እንደሚቆሙ ማረጋገጫና መተማመኛ መስጠት ይቻላል ወይ? ትልቁ ጥያቄ ነው። ምክንያቱም በአፍ ሊባል ይቻላል፤ ፎቶ መነሳት፣ ስብሰባዎችን ማድረግ ቀላል ነው፤ መሬት ላይ የወረደ ዘላቂ ግንኙነት ግን ወደ ህዝብ መውረድ አለበት" ይላሉ።
አቶ አበበ ይርጋ፤ “የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚ የሚሆነው በጦርነቱ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የተሳተፉና ሰለባ የሆኑ አካላት መሳተፍ ሲችሉ ነው” ሲሉም ይናገራሉ።
ጦርነቱ እንዳያገረሽ እንደ ኤርትራ አይነት ያሉ ወገኖች መሳተፍ ወሳኝ ነው ሲሉ የሰላም ስምምነቱ በሁለቱ ፈራሚዎች ቅቡልነት ብቻ የሚፈጸም አይደለም በማለት ይሞግታሉ።
በጦርነቱ የተሳተፉ ወገኖች መወያየታቸው፣ አካሄዱን መረዳታቸው፣ ማወቃቸው ሰለሚያስፈልግ ጉብኝቱ ለኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ጥሩ ነገር ይፈጥራል ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል።
ኤርትራ በሰላም ስምምነቱ ተሳታፊ ባትሆንም "የውጭ ኃይሎች" የሚለው አገላለጽ ኤርትራን ለማመልከት እንደሆነ የሚጠቅሱት ተንታኙ፤ ሰላማዊ ሁኔታ ለመፍጠር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ በዚህ ጉብኝት ውይይት ይደረጋል ብለው ይጠብቃሉ።
ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ኤርትራ የጥቃት ሰለባ ከመሆን ባለፈ ወታደሮቻን አሰማርታ ተዋግታለች ከዚህም ባሻገር ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማ ይነገራል። ባለፈው ታህሳስ 2015 ዓ.ም. በተደረሰው የሰላም ስምምነት ሀገሪቱ ደስተኛ አይደለችም የሚሉ ተንታኞች የሀገራቱ ግንኙነት ሻክራል ይላሉ። ምንም እንኳ የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ባይስማም።
ሰሞነኛ የጦር አዛዦች ጉብኝት ምን ያህል የሀራቱን ግንኙነት ያነቃቃል? የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አበበ ይርጋ፤ የሀገራት ግንኙነት መስመር ሚይዘው በህግ ማዕቀፍ ሲደገፍ ነው፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ግን ምን ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ግልጽ አይደለም ይላሉ፡፡ የሀገራቱ ግንኑነት ተቋማዊና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን 'የሁለት ግለሰቦች' ከሚመስል ግንኙነት መወጣት እንዳለበት ያሰምራሉ።
የሀገራቱ ግንኙነት መርህ ላይ ካልተመሰረተ ኮሽ ባለ ቁጥር የሚደበዝዝ እንደሚሆን በመናገር አሁንም ስጋት እንዳለ የሚያነሱት አበበ ይርጋ፤ ፍላጎትና ጥቅምን የለየ ግንኙነት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።