ኢጋድ በ2007 ኬንያ የኢትዮ- ኤርትራን የድንበር ውዝግብ እንድትመለከት ውሳኔ ሲያሳልፍ ኤርትራ ከድርጅቱ አባልነቷ መውጣቷ ይታወሳል
ኤርትራ ከ16 አመት በኋላ ወደ ምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አባልነቷ ተመለሰች።
በትናንትናው እለት በጂቡቲ በተካሄደ ስብሰባም ኤርትራ የኢጋድ መቀመጫዋን ዳግም መረከቧን የሀገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ባለፉት 16 አመታት ከምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ተነጥላ የቆየችው ሀገር ለቀጣናው ሰላም፣ መረጋጋትና ትብብር በቁርጠኝነት እንደምትሰራም ነው ያስታወቁት።
ኤርትራ ኢጋድ ውጤታማ ስራን እንዲያከናውን ከሰባቱ አባል ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት መዘጋጀቷንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፈው አመት በኬንያ ጉብኝት ሲያደርጉ ሀገራቸው ወደ ኢጋድ እንደምትመለስ ማሳወቃቸው ይታወሳል።
በትናንትናው እለት በጂቡቲ በተካሄደው ስብሰባ ላይም ይገኛሉ ተብሎ ቢጠበቅም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን ኦስማን ሳሌህ እና አማካሪያቸውን የማነ ገብረአብ ልከዋል።
የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ዶክተር ወርቅንነህ ገበየሁ፥ ኤርትራ ወደ ኢጋድ ዳግም መመለሷን አድንቀዋል።
ኤርትራ በፈረንጆቹ 2007 ኬንያ የኢትዮ-ኤርትራን የድንበር ውዝግብ እንድትመለከት የውሳኔ ሃሳብ ማውጣቱን ተከትሎ ከኢጋድ አባልነቷ መውጣቷ የሚታወስ ነው።
ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር በ2018 የሰላም ስምምነት መድረሷን ተከትሎም ከጎረቤቶቿ እና ከቀጠናዊ ድርጅቶች ጋር ትብብሯን ዳግም እየጀመረች ነው ተብሏል።