ኤርትራ ወታደሮቿ በሰሜኑ ጦርነት ወንጀል ፈጽመዋል ሚለውን የአሜሪካ ውሳኔ ውድቅ አደረገች
አሜሪካ ፤ በሰሜን ኢትየጵያ ለተፈጸሙ ወንጀሎች የኤርትራ ኃይሎችም ጭምር ተጠያቂ መሆናቸው ገልጻለች
ኤርትራ፤ እየተካሄደ ያለውን ርካሽ “የማሰይጠን ዘመቻ” ኤርትራ እና ኢትየጵያን በውሸት ለመወንጀል ያለመ ነው ብላለች
አሜሪካ ለሁለት አመታት በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያው ደም አፋሳሽ ጦርነት ዙሪያ ሰኞ እለት ይፋ ባደረገቸው ሪፖርት የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ እና የአማራ ኃይሎች በጦርነቱ “በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል” መፈጸማቸውን ማስታወቋ አይዘነጋም፡፡
- የኤርትራ ወታደሮች አሁንም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንደሚገኙ አሜሪካ ገለጸች
- የኤርትራ ወታደሮች አሁንም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንደሚገኙ አሜሪካ ገለጸች
- የሩሲያው ከፍተኛ ዲፕሎማት እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ያነሷቸው አንኳር ጉደዮች ምንድን ናቸው?
በተጨማሪም የህወሓትን ጨምሮ ሁሉም ተፋላሚ ኃይሎች “የጦር ወንጀል” ፈጽመዋል ስትል ገልጻለች፡፡
ሪፖርቱን ይፋ ያደረጉት የአሜሪካው ከፍተኛ ዲፕሎማት አንቶኒ ብሊንከን “ከነዚህ ወንጀሎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ድንገት ወይም በጦርነት የተከሰቱ ብቻ ሳይሆኑ ታስቦ እና ሆን ተብሎ የተፈጸሙ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
መስራቤታቸው ህጎችን እና እውነታውን በጥንቃቄ ካጤነ በኋላ ሁሉም ተፋላሚ ኃይሎች በሰሜን ኢትየጵያው ጦርነት የጦር ወንጀሎችን መፈጸማቸውን በተመለከተ ድምዳሜ ላይ መድረሱም ገልጸዋል ብሊንከን፡፡
አሜሪካ ይህን ትበል እንጅ የኢትዮጵያ መንግስት በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫው በአሜሪካው ከፍተኛ ዲፕሎማት የቀረበውን ሪፖርት ውድቅ አድርጎታል፡፡
የአሜሪካ መግለጫ “አዲስነት የሌለውና ጊዜውን ያልጠበቀ” ነው በሚል ተቃውሞታል፤የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፡፡
“ኢትዮጵያ የተሽፋፈነ ውግዘትን አትቀበልም” ያለው መግለጫው፥ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርትን ተመርኩዞ የወጣው አዲስ መግለጫ ምንም አዲስ ነገር እንደሌለውም ጠቁሟል።
የአሜሪካ መግለጫ ያስቀመጠው ወቀሳ ሚዛን የሳተና (የህወሃት ሃይሎችን) የወንጀል ተጠያቂነት “መርጦ” ለመቀነስ ጥረት ያደረገ ስለመሆኑም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ያመላከተው።
እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በጦርነቱ ተፈጽመወል በተባሉ ወንጀሎች እጅ አላት የተባለችው ኤርትራ ሪፖርቱን ውድቅ አድርገዋልች፡፡
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ በአሜሪካ ቀረበው ክስ መሰረት ቢስ እና ማስረጃ የሌለው የስም ማጠልሸት ነው ሲል ተቃውሞታል፡፡
አሁን እየተካሄደ ያለውን ርካሽ “የማሰይጠን ዘመቻ” ኤርትራን እና የኢትየጵያ መንግስትትን በውሸት ውንጀላ በማጥላላት እና በማሸማቀቅ እንዲሁም በተቃራኒው ህወሓትን በማጠናከር ተጨማሪ ትርምስ ለመፍጠር ያለመ ነውም ብሏል መግለጫው፡፡
ደም አፋሳሹ ሰሜን ኢትዮጵያው ጠርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት የቀጠፈ እንዲሁም ሚሊዮኖችን ለመከራና ሰቆቃ የዳረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት በሚል በአፍሪካ ህብረት አዳረዳሪነት በመንግስት እና በህወሓት መካከል ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ በፕሪቶሪያ መፈረሙም ይታወሳል፡፡