ፕሬዝደንት ኢሳያስ በአሜሪካ እና ኔቶ የበላይነት የሚመራው የርዕዮተ ዓለም የበላይነት እየተንኮታኮተ መሆኑንም ገልጸዋል
የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ "አዲስ የዓለም ስርዓት ወይም ኒው ወርልድ ኦርደር የሚፈጥርበት የሽግግር ወቅት ላይ ነን" ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዝደንቱ ይህን ያሉት ከሩሲያው አርቲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።
ኘሬዝደንቱ ይህ የሽግግር ወቅት በስኬት ይታለፋል ብለዋል።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ በአሜሪካ እና ኔቶ የበላይነት የሚመራው የርዕዮተ ዓለም የበላይነት እየተንኮታኮተ መሆኑንም ገልጸዋል።
አዲስ የዓለም ስርአት እንዲፈጠር ሩሲያ ወሳኝ ሚና አላት የሚሉት ፕሬዝደንቱ በሩሲያ ላይ የሚደርሰውን ውግዘትም ይሁን ጦርነት እንደማይቀበሉት ተናገረዋል።
ኤርትራ፣ ተመድ ሩሲያ ዩክሬንን ወርራለች ብሎ ሲያወግዝ ከተቃወሙት ሀገራት መካከል አንዷ ነቀረች።
ፕሬዝደንት ኢሳያሳ፣ ሩሲያ በዩክሬን የወሰደችውን እርምጃ ራስን የመከላከል ተግባር ነው በሚል ይደግፉታል።
እንደፕሬዝደንት ኢሳያስ ገለጻ ሩሲያ እየተዋጋች ያለችው አለምን በበላይነት ለመምራት ከሚፈልገው ርዕዮተ ዓለም ጋር መሆኑን እና ሁሉም ሊደግፈው የሚገባ ነው ብለዋል።
ይህን የርዕዮተ ዓለም የበላይነት ሁሉም ሀገራት መዋጋት አለባቸው ያሉት ኘሬዝደንቱ በመከባበር ላይ የተመሰረተ ለብዙ ሀገራት ግንኙነት ወይም ለመልቲላተራሊዝም የሚመች አዲስ የዓለም ስርዓት መፈጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ይህን ርዕዮተ ዓለም የማይከተሉ ሀገራት ማዕቀብ እና ውግዘት ይደርስባቸዋል፤ይህ መቀየር አለበት ሲሉም ተናግረዋል ፕሬዝደንቱ።
ኤርትራ ማዕቀብ የተጣለባት በአሜሪካ ለሚመራው ርዕየተ ዓለም ባለማጎብደዷ ነው ብለዋል ፕሬዝደንቱ።
በአንድ ቡድን የበላይነት የሚመራ ርዕየተዓለም ማብቃት አለበት ያሉት ፕሬዝደንት ኢሳያስ ሀገራት በአጋርነት አዲስ የዓለም ስርዓት መፍጠር ይችላሉ ብለዋል።
ዓለም በአንድ ርዕዮተ ዓለም እንድትመራ የሚሞክረው ርዕየተ ዓለም "የጫካ ስርዓት" መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንት ኢሳያስ ይህ ሙከራ ታሪክ መሆን አለበት ብለዋል።
ፕሬዝደንቱ ይህ በአንድ ርዕዮተዓለም የሚመራው የዓለም ስርአት የሚቀየረው በአጋርነት መሆኑን ገልጸዋል።
ስትራቴጂካዊ በሆነው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ያለችው ኤርትራ ከሩሲያ እና ከቻይና ጋር በማበር የእነአሜሪካ የበላይነት እንዲከስም ትፈልጋለች።
ቻይና እና ሩሲያ በኤርትራ ላይ አይናቸውን ጥለዋል።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ በቅርቡ ሁለቱን የእስያ ኃያላን (ቻይና እና ሩሲያን) መጎብኘታቸው ይታወሳል።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ ቻይናን ከጎበኙ ሁለት ሳምንት በኋላ ሩሲያን በፕሬዝደንት ፑቲን ግብዣ ጎብኝተው ነበር።