የእስራኤል ድርጊት ራስን ከመከላከልም ያለፈ እንደሆነ ቻይና ገለጸች
እስራኤል ጋዛን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር የምድር ላይ ዘመቻ እንደምትጀምር አስታውቃለች
ኢራን በበኩሏ እስራኤል በንጹሀን ላይ የምታደርገውን ዘመቻ ካላቆመች ጦርነቱን ልትቀላቀል እንደምትችል ገልጻለች
የእስራኤል ድርጊት ራስን ከመከላከልም ያለፈ እንደሆነ ቻይና ገለጸች።
ለፍልስጤም ነጻነት እየተዋጋ መሆኑን የሚገልጸው ሀማስ ከስምንት ቀን በፊት በእስራኤል ላይ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ አዲስ ጦርነት ተቀስቅሷል።
እስራኤል ራሴን እየተከላከልኩ ነው በሚል የሀማስ ይዞታዎች ናቸው ባለቻቸው ቦታዎች ላይ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻዋን ቀጥላለች።
የእስራኤልን ጥቃት ተከትሎ ንጹሀን ዜጎች እና አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች የጥቃቱ ዋና ኢላማ ሆነዋል የሚሉ ትችቶች በተመድ እና የተለያዩ ሀገራት እየተነሳ ይገኛል።
የቻይና ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዋንግ ዪ ከሳውዲ አቻቸው ፈይሰል ቢን ፋርሀን አል ሳውዲ ጋር በስልክ ስለ እስራኤል-ሀማስ/ፍልስጤም ጦርነት ዙሪያ መወያየታቸውን ሲጂቲኤን እና አርቲ ዘግበዋል።
እንደዘገባው ከሆነ ቻይና የእስራኤል ድርጊት ራስን ከመከላከል ያለፈ እንደሆነ ታምናለች ተብሏል።
በመሆኑም እስራኤል በሀማስ ጥቃት ምክንያት መላው ፍልስጤማዊያንን ከመጉዳት እንድትታቀብ ዋንግ ዩ አስጠንቅቀዋል ተብሏል።
ሚንስትሩ አክለውም ቻይና የንጹሀንን ጉዳት በጽኑ ታወግዛለች ያሉ ሲሆን ጦርነቱ ቆሞ አለመግባባቱ በድርድር እንዲፈታም ትፈልጋለች ተብሏል።
ኢራን በበኩሏ እስራኤል በሀማስ ስም በመላው ፍልስጤማዊያን ላይ እያደረሰች ያለውን የከፋ ጥቃት እንድታቆም አሳስባለች።
የኢራን ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሁሴን አሚራብዶልሀሚን ለተመድ የመካከለኛው ምስራቅ አምባሳደር እንዳሉት "እስራኤል በጋዛ ንጹሀን ላይ የምታደርገውን የንጹሀን ግድያ ካላቆመች ኢራን ጦሯን ወደ ጋዛ ልትልክ ትችላለች" ሲሉ ተናግረዋል ተብሏል።
በእስራኤል-ፍልስጤም ጦርነት እስካሁን የተገደሉ ዜጎች ቁጥር አምስት ሺህ ማለፉ ሲገለጽ የቆሰሉ ሰዎች ደግሞ ከ15 ሺህ በላይ መድረሱ ተገልጿል።