በኤርትራ የሚገኙት የሶማሊያ ወታደሮች በሚቀጥሉት ቀናት ወደ ሀገራቸው መመለስ ይጀምራሉ- የሶማሊያ ፕሬዝዳንት
ሶማሊያውያን ወታደሮች ወደ ሀገራቸው መመለስ ሼህ ማህሙድ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ከገቡት ቃል ውስጥ አንዱ ነው
5 ሺህ የሶማሊያ ወታደሮች በኤርትራ ምድር ስልጠና እየወሰዱ እንደሆነ ይነገራል
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ በኤርትራ ለወራት ሲሰለጥኑ የቆዩት የሶማሊያ ወታደሮች በሚቀጥሉት ቀናት ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደሚጀምሩ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት ለአሜሪካ-አፍሪካ ጉባኤ ወደ ዋሽንግተን ባቀኑበት ወቅት በአሜሪካ የሚኖሩ ሶማሊያውያን ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ ሲሆን "ወታደሮቹ ከታህሳስ ወር መጨረሻ በፊት መመለስ ይጀምራሉ፤ በጥር ወር መመለሻቸው ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል" ብለዋል ።
"ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ዝግጅቶችን ሁሉ አጠናቀናል እናም አላህም ቢፈቅድ ከዚህ በኋላ የሚዘገይ ነገር የለም" ሲሉም አክለዋል ፕሬዝዳንቱ ፡፡
በኤርትራ የሚገኙትን ሶማሊያውያን ወታደሮች ወደ ሀገራቸው መመለስ ሼህ ማህሙድ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ከገቡት ቃል ውስጥ አንዱ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በዚህም በወርሃ ሃምሌ በኤርትራ ባደረጉት የአራት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ወታደሮቹ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበት ጊዜ ሩቅ እንዳማይሆን ፍንጭ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከጉብኝቱ መልስ ከተወሰኑ ወላጆች ጋር ባደረጉት ውይይት ኤርትራ ወደሚገኘው ማሰልጠኛ ማእከል ሄደው በስፍራው የሚገኙ የሶማሊያ ወታደሮች መጎብኘታቸውን ተናግረው ነበር፡፡
ፕሬዝዳንቱ ወላጆቹን “ የደስታ ቀናት እየመጡ ነው” ሲሉም ነበር የተናገሩት በወቅቱ፡፡
ለስልጣን በሚል ወደ ኤርትራ የተላኩት የሶማሊያ ወታደሮች ጉዳይ በርካታ ሶማሊውያን እናቶች ያስጨነቀ አጀንዳ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ሶማሊያም ሆነች ኤርትራ ለረዥም ጊዜ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበው የነበረ ቢሆንም ፤ በቅርቡ ከስልጣን የተሰናበቱት የቀድሞ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፋርማጆ ለአዲሱ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ባስረከቡበት ወቅት 5 ሺህ የሶማሊያ ወታደሮች በኤርትራ ምድር ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸው ለመጀመሪያ ጊዜ መናገራቸው ይታወሳል፡፡