ኢትዮጵያ ሲፈለግ የነበረውን ኤርትራዊ ተጠርጣሪ ለጣልያን አሳልፋ መስጠቷ ተገለጸ
ተመስገን ገብሩ የተባለው ይህ ተጠርጣሪ በህገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል ይፈለግ ነበር
ባለፈው ሳምንት አንድ ተመሳሳይ ተጠርጣሪ ለሆላንድ ፖሊስ መተላለፉ ይታወሳል
ኢትዮጵያ ኤርትራዊውን ተጠርጣሪ ለጣልያን ፖሊስ አሳልፋ መስጠቷ ተገለጸ።
ኢትዮጵያ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በኢንተር ፖል ይፈለግ የነበረውን ዋና ኤርትራዊ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ በመያዝ አሳልፋ መስጠቷ ተገልጿል።
ተመስገን ገብሩ ገብረመድህን የተባለው ኤርትራዊ ተጠርጣሪ በህገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል በጣልያን መንግስት ተፈላጊ እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።
ዘገባው አክሎም ተጠርጣሪው ግለሰብ የ35 ዓመት እድሜ ያለው ሲሆን አፍሪካዊያን ስደተኞችን በሰሜን አፍሪካዋ ሊቢያ በኩል በህገወጥ መንገድ ዜጎችን በማጓጓዝ ወደ አውሮፓ እንዲገቡ ያደርጋል የሚል ክስ ቀርቦበታል።
ተጠርጣሪው ስደተኞችን በማሰቃየት፣ አካል በማጉደል እና ሌሎች ተያያዥ ወንጀሎችን በመፈጸም በመፈለግ ላይ መሆኑን አውቆ ተደብቆ እንደነበር ተገልጿል።
ግለሰቡ በኢትዮጵያ ተደብቆ እየኖረ እያለ ተይዞ ለጣልያን ፖሊስ ተላልፎ መሰጠቱን ዘገባው የጣልያን ፍትህ ሚንስቴር በምንጭነት ጠቅሶ ዘግቧል።
ጣልያን ከፈረንጆቹ 2020 ጀምሮ በከባድ ወንጀል ስትፈልገው የነበረው ይህ ተጠርጣሪ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በኩል ተላልፎ ተሰጥቷል ተብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባሳለፍነው ሳምንት ሌላኛውን የህገወጥ ሰዎች ዝውውር ተጠርጣሪ ወንጀለኛ ለሆላንድ መንግሥት አሳልፋ መስጠቷ ይታወሳል።