“የኤርትራ ሰራዊት ከኢትዮጵያ መውጣት ለዘላቂ ሰላም ቁልፍ ሚና አለው”- አሜሪካ
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ጋር መወያየታቸውን አስታውቀዋል
አንቶኒ ብሊንክንና ጠ/ሚ ዐቢይ በኦሮሚያ ክልል እየታየ ያለው አለመረጋጋት እንዲቆምም ተወያይተዋል
የኤርትራ ሰራዊት ከሰሜን ኢትዮጵያ መውጣት መጀመሩ ለዘላቂ ሰላም ጠቃሚ መሆኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አስታወቁ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ መወያየታቸውን አስታውቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ “የተኩስ አቁም ስምምነትን ተከለትሎ እስካሁን በታዩ መሻሻሎች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ተወያይቻለሁ” ብለዋል።
- የኤርትራ ሰራዊት እንቅስቀሴ ስጋት የፈጠረባቸው የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ምን እያሉ ነው?
- “የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ መቼ ይወጣል?” ተብለው የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ምን አሉ?
“የኤርትራ ወታደሮች ከሰሜን ኢትዮጵያ መውጣት መጀመራቸውም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ተስፋ ሰጪ እርምጃ” መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታወቀዋል።
ውይይቱ አስመልክቶ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ኔድ ፕራይስ በሰጡት መግለጫም፤ አንቶኒ ብሊንከን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመንግስት እና በህወሓት መካከል በተፈረመው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ላይ ተወያይተዋል ብለዋል
በውይይታውም በሰላም ስምምነቱ አፈጻም የእስካሁን ሂደት መሻሻሎች መታየቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አስታውቀዋል ሲሉ ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ የሰብዓው መብት ተቆጣጠሪ አካላት ጦርነት ወደነበረባቸው አካባቢዎች የሚገቡበት ሁኔታ እንዲመቻች ማሳሰባቸውንም አስታውቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የሰላም ሂደት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗንም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
ሌላው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተወያዩበት ጉዳይ በኦሮሚያ ክልል ባለው አለመረጋጋት ላይ መሆኑንም ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።
በኦሮሚያ ክልል እየታየ ያለው አለመረጋጋት በፍጥነት የማቆም አስፈላጊነት ላይ መወያየታቸውንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
በህዳር ወር 2015 መንግስት በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የሁለት አመቱ ደም አፋሳሽ ጦርነት መቆሙ ይታወሳል።
ከሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ውጪ የሆኑ የአጎራባች ክልሎች እና የውጭ ኃይሎች ከትግራይ ክልል መውጣት እንዳለባቸው በሰነዱ ላይ መጠቀሱም አይዘነጋም።
እስካሁን የኤርትራ ስራዊት መውጣትን በተመለከተ በየትኛውም ወገን ማለትም በፌዴራል መንግስት፣በህወሓት እንዲሁም በኤርትራ በኩል በይፋ የተባለ ነገር የለም።
ነገርግን የሰላም አደራዳሪው ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ሰሞኑን ከፋይናንሻል ታይምስ ጋር በነበራቸው ዘለግ ያለ ቆይታ “የኤርትራ ሰራዊት ያለው በድንበር አከባቢ ነው” ማለታቸው አዲስ ነገር እንደነበር ይታወሳል።
የሰላም አዳራደሪው ኦባሳብጆን እና ጌታቸው ረዳን መረጃ መነሻ በማድረግ አል-ዐይን አማርኛ የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን ያናገረ ሲሆን የኤርትራ ሰራዊት ከተለያዩ ቦታዎች መንቀሳቀስ የጀመረው ጥር 11 ቀን 2015 ዓ.ም መሆኑ ለማረጋገጥ ችሏል።
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአክሱም ከተማ ነዋሪ የኤርትራ ወታደሮችን የጫኑ 700 ገደማ ያህሉ ተሸከርካሪዎች ከአድዋ አቅጣጫ በመምጣት በአክሱም በኩል ወደ ሽሬ ሲያልፉ ማየታቸው ተነግሯል።
በቅርቡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኤርትራ ወታደሮች ከነ ወታደራዊ ሎጂስቲካቸው ወደ አድዋ አቅጣጫ አልፈው እንደነበር ያስታወሱት ነዋሪው፤ የአሁኑ እንቅስቀሴ ያልጠበቁት መሆኑም ገልጸዋል።