“የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ መቼ ይወጣል?” ተብለው የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ምን አሉ?
ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ የሶስትዮሽ ውይይቱም እንዲቀጥል እንደምትፈልግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ
ኢትዮጵያ ወደ አግዋ እድል ለመመለስ ለአሜሪካ ጥያቄ ማቅረቧን አምባሳደር መለስ አስታውቀዋል
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዋሽንግተን እየተካሄደ ያለው የአፍሪካ-አሜሪካ የመሪዎች ጉባኤ፣ የኤርትራ ጦር በኢትዮጵያ፣ የጎረቤት ሀገራት ዲፕሎማሲ፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ፣የህዳሴው ግድብ ጉዳይ እና ሌሎችም ሀሳቦች በመግለጫው ላይ ተነስተዋል።
ቃል አቀባዩ ከጋዜጠኞች ከቀረበላቸው ጥያቄዎች መካከል በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለው የኤርትራ ጦር መቼ ይወጣል? የሚለው አንዱ ነበር።
አምባሳደር መለስም በሰጡት ምለሽ፤ " የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ የሚወጣው የፌደራል መንግሥት እና ህወሀት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተስማሙት እና ኬንያ ናይሮቢ ቀጥሎ በተካሄደው ውይይት መሰረት ነው። ሌላው የሚወራው ሁሉ የጎንዮሽ ወሬ ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የኤርትራ ጦር እና የህወሀት ትጥቅ መፍታት ጎን ለጎን እንደሚከናወኑ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት መገለጹ ይታወሳል።
አምባሳደር መለስ በዋሸንግተን እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ- አሜሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳድር በተደረገላቸው ግብዣ መሰረት መሆኑንም አክለዋል።
በጠቅላይ ሚንስትሩ የሚመራው የኢትዮጵያ ልኡክም ከአሜሪካ፣ የአፍሪካ እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጋር እየተወያየ መሆኑንም አምባሳደር መለስ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከአሜሪካ ቀረጥ ነጻ እድል ወይም አግዋ ታግዳ ነበር ያሉት አምባሳደር መለስ ወደ ዚህ እድል ዳግም ለመመለስ ለአሜሪካ መሪዎች ጥያቄ መቅረቡን ተናግረዋል።
የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ባሳለፍነው ሳምንት በሳውዲ አረቢያ በተካሄደው የአረብ-ቻይና ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ላይ ወደ አሳሪ ስምምነት እንድትመጣ በሚል ላቀረቡት ጥያቄም ቃል አቀባዩ ምላሽ ሰጥተዋል።
"ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ዘመን የተደረጉ ስምምነቶችን አትቀበልም፣ የሶስትዮሽ ውይይቱም እንዲቀጥል ትፈልጋለች፣ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ ስምምነቶችን እና ውይይቶችን ለማድረግ ዝግጁ ነን" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል አምባሳደር መለስ።
ቃል አቀባዩ አክለውም ህገወጥ የሰዎች ዝውውር የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ እያበላሸ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይም ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ከአዲስ አበባ-ናይሮቢ-ዳሬሰላም- ሉሳካ እና ጆሀንስበርግ ድረስ ሰንሰለት ያለው ነው ተብሏል።
በመሆኑም በዚህ የህገወጥ ሰዎች ዝውውር ሰንሰለት የተናጥል ሳይሆን የብዙ ሀገራትን ትብብር የሚጠይቅ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ በማላዊ እና ዛምቢያ ህይወታቸው አልፎ የተገኙት ኢትዮጵያዊያን ጉዳይም በዚህ የሚታይ እንደሆነም አምባሳደር መለስ በመግለጫው ላይ ተናግረዋል።