ከሰሞኑ በምስራቅ አፍሪካ እየታየ የሚገኝው ውጥረት ምን ያህል አስጊ ነው?
“በአፍሪካ ቀንድ የትብብር መንፈስ አለመኖር ሀገራት በጥርጣሬ እንዲተያዩ አድርጓል”- ምሁራን
አል ዐይን አማረኛ ያነጋገራቸው የውጭ ግንኙነት ምሁራን የሶማሊያ አካሄድ በቀጠናው ተጨማሪ ውጥረትን ከማባበስ ባለፈ ለጥያቄዋ መልስ የማያስገኝላት እንደሆነ ተናግረዋል
ተሰባሪ ነው የሚባለው የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላም ባለፉት አመታት ከጥይት ደምጽ ሙሉ ለሙሉ ተላቆ አያውቅም።
ቀጠናው በአለም አቀፍ ጂኦፖሎቲክስ ካለው ቁልፍ ሚና አንጻር ከአካባቢው ራቅ ያሉ ሀያላን ሀገራት ጭምር ፍላጎት የሚንጸባረቅበት፣ አንዱ ከሌላው የተሻለ ጥቅሙን አስጠብቆ ለመጓዝ የሚሽቀዳደምበት የአለም ክፍል እንደሆነ ይነገራል።
የአለም 12 በመቶ ወይም አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚያወጣ የንግድ መተላለፍያ የሆነው ቀይ ባህር ይህን ቀጠና ተጎራብቶ መገኝቱ ደግሞ ስትራቴጂካዊ ስፍራ እንዲሆን ካስቻሉት ወሳኝ ነጥቦች መካከል አንዱ ነው።
120 ሚሊየን ህዝብ ባለቤት እንደሆነች የሚነገርላት ኢትዮጵያ የህዝቦችን ጥያቄ ለመመለስ እና ለደህንነቴ ዋስትና ለመስጠት እራሴ የማስተዳድረው ወደብ ያስፈልገኛ በሚል መነሻ ከራስ ገዟ ሃገር ሶማሊላንድ ጋር የወደብ የመግባብያ ስምምነት ተፈራርማለች።
ይህን የወደብ ስምምነት ሉአላዊነቴን እንደመዳፈር ነው ያለችው ሶማሊያ በበኩሏ ስምምነቱን በመቃወም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ ትገኛለች።
ይህን ተከትሎም የሀገሪቱ ፕሬዝዳነት ሀሰን ሼክ መሀመድ ስምምነቱ ከተፈረመ ወዲህ ዲፒሎማሲያዊ አጋርነትን ፍለጋ ወደ አስመራ እና ካይሮ እንዲሁም ወደ ሌሎች ሀገራት በመመላለስ ድጋፍን ለማሰባሰብ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።
ፕሬዝዳንቱ ከሳምንታት በፊት ከግብጽ ጋር ወታደራዊ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ካይሮ ሁለት ወታደራዊ እቃ ጫኝ አውሮፕላኖችን መሳርያዎችን አሸክማ ወደ ሞቃዲሾ ልካለች።
ከዚህ ባለፈም በመጪው ዓመት ጥር ወር የሚጠናቀቀው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ)ን በሚተካው አዲሱ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በተለያዩ ጊዜያት የሚሰማሩ 10 ሺህ ወታደሮችን ለማሰማራት ግብጽ ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች።
ይህንን ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል ሲል የከሰሰው የኢትዮጵያ መንግስት ኢትዮጵያ ሁኔታውን አጇን አጣጥፋ እንደማትመለከት አቋሙን ገልጿል።
በነዚህ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሰሞኑ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ከፍ ያለ ውዝግብ እና ውጥረት ውስጥ ይገኛል።
ለመሆኑ አሁናዊ ቀጠናዊ ውጥረቶች ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ቀንድ ስጋት የመሆን እድላቸው ምን ያህል ነው? ኢትዮጵያስ ስጋቱን በምን አይነት መንገድ መከላከል እና ዝግጅት ማድረግ አለባት? አል ዐይን አማረኛ የውጭ ጉዳይ ግንኙት ምሁራንን አነጋግሯል።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ዶክተር ዳርእስከዳር ታየ በአፍሪካ ቀንድ የትብብር መንፈስ አለመኖር ሀገራት በጥርጣሬ እንዲተያዩ አድርጓል ይላሉ።
“ወደብንም ሆነ ወንዝን የአንዱን ጥቅም በማይነካ መልኩ አልምቶ መጠቀም ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ከመፍጠሩም በላይ እንደ አፍሪካ ባሉ በርካታ ደሀ ሀገራት በሚገኙባቸው የአለም ክፍሎች ወጪን ለመቆጠብ እና ትብብርን ለማጽናት የሚረዳ ነው” ሲሉ ይናገራሉ።
በተጨማሪም “ሶማሊያ አሁን በምትገኝበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የወደብ ስምምነት መፈራረሟ ሉአላዊነቴን የሚጋፋ ነው በሚል ሊያስበረግጋታት የሚገባ ጉዳይ አይደለም፤ ምክንያቱም ራስ ገዟ ሀገር ሙሉ ሀገር ለመሆን እንቅስቃሴ ከጀመረች ሰንባብታለች እንደውም ከሶማሊያ የተሻለ ሀገር የመሆን ቁመና ላይ የምትገኝው ሶማሊላንድ ነች” ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ግንኙነት ተመራማሪው ሲቀጥሉ ሶማሊያ በምትለው ልክ ሉአላዊነቴ ተጥሷል የሚል እስቤ ቢኖራት እንኳን አሁን እየሄደችበት የምትገኝው አካሄድ በቀጠናው ተጨማሪ ውጥረትን ከማባበስ ባለፈ ለጥያቄዋ መልስ የማያስገኝላት እንደሆነ ያነሳሉ።
ባለፉት አስርት ዓመታት የአልሸባብ መፈርጠም ለእኔም ስጋት ነው በሚል የሞቃዲሾ መንግስትን ስታግዝ የቆየችው ኢትዮጵያ ሶማሊያ አሁን ለመዛመድ ጥረት እያደረገች ከምተግኝባቸው ሀገራት በተሻለ ስትራቴጂካዊ አጋር ሆና መዝለቋንም አክለዋል።
ግብጽን በተመለከተ ካይሮ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ልዩነት በርትቶባታል ውስጣዊ አንድነትም ተቀዛቅዟል ብላ ባሰበች ጊዜ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጻረሩ ተግባራትን ከመፈጸም ተቆጥባ አታውቅም የሚሉት ዶክተር ዳርእስከዳር ይህ ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ እና በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ የበላይ ሆኖ ከመዝለቅ የሚመነጭ እንደሆነ ይናገራሉ።
“ግብጽ እና ኢትዮጵያ ከአክሱም ዘመን ጀምሮ በባህል ፣ በሀይማኖት እና በታሪክ የበላይ ሆኖ ለመዝለቅ ባላቸው ፉክክር በመሀሉ የአባይ ወንዝ አለ።
ግብጾችን ቅኝ ግዛት የገዙት እንግሊዛውያን አባይን መቆጣጠር ምስራቅ አፍሪካን መቆጣጠር የሚል ትርክት ያሰረጹባት ካይሮ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚገዳደሩ ድርጊቶችን መፈጸሟ አያስገርምም” ባይ ናቸው።
ከዚህ ባላፈም “አልሸባብን ለመዋጋት እልህ አስጨራሽ ትግል በሚደረግበት ወቅት አንድም የረባ እንቅስቃሴ አድርጋ የማታውቀው ግብጽ ዛሬ ከሶማሊያ መንግስት ጋር የተፈጠረውን ልዩነት መነሻ አድርጋ ወደ ቀጠናው መቅረቧ የኢትዮጵያን ፍላጎት ለማጨናገፍ በተጻራሪ ለመቆም ካልሆነ ለሀሰን ሼክ መንግስት ወዳጅነቷን ለማሳየት አይደለም” ብለዋል።
የኢንተራክሽን ፎር ቼንጅ ኢን አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ወርቁ ያቆብ በበኩላቸው፤ በቀጠናው የአረብ ሀገራትን ጨምሮ የምዕራባውያን ሀያላን ከፍተኛ ፍላጎት መኖር ከአካባቢው ጋር የሚገናኙ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ የሚደረጉ ሙከራዎች ቀላል እንዳይሆኑ እንደሚያደርጉ ነግረውናል።
“ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሀገር ሶማሊላንድ ጋር የወደብ ስምምነት ከማድረጓ በፊት ከሌሎች ሀገራት ወደብ ለማግኝት ምን ያህል ጥረት እንዳደረገች አላውቅም፤ ነገር ግን 120 ሚሊየን ህዝብ ባለቤት ሆና እራሴ የማስተዳድረው ወደብ ይኑረኝ ብላ መነሳቷ ተገቢ ነው ብየ አምናለሁ” ብለዋል።
“ይሁንና አካባቢው ላይ ካሉ ጠንካራ ፍላጎቶች አንጻር መሰል ተቃርኖውች ማጋጠማቸው ተጠባቂ ነው። በኤደን ባህረ ሰላጤ እና በቀይ ባህር ዙርያ ኢትዮጵያ የባህር ሀይል ቢኖራት ጥቅማችን ይነካል አልያም የሀገሪቷን ሁለንተናዊ አቅም ያሳድጋል የሚሉ እንደ ግብጽ ያሉ ሀገራት መነሳታቸውም ለዚሁ ነው” ብለውናል፡፡
ዶክተር ወርቁ ሲቀጥሉም ከግብጽ ጀርባ የራሳቸው ፍላጎት ያለቸው ሀገራት መኖራቸውንም መዘንጋት እንደሌለበት አሳስበው በአባይ ጉዳይ ያነሳችው እጀንዳ ያለቀባት የምትመስለው ካይሮ በሶማሊያ ጉዳይ ጠንካራ ተገዳዳሪ ልትሆን እንደምትችል አስምረው ተናግረዋል።
የብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የሚደረጉ ጥረቶች ከፈተናዎች ጋር የሚመጡ ናቸው የሚሉት ዶክተር ወርቁ ዋናው ፈተናዎችን የምናልፍበት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና የዲፕሎማሲ ጥበብ ዋሳኝ እንደሚሆን ያነሳሉ፡፡
ለመሆኑ የግብጽ ወደ አካባቢው መጠጋት ለቀጠናው እና ለኢትዮጵያ ምን ያህል ስጋት ነው ?ብለን የጠየቅናቸው ዶክተር ወርቁ ያቆብ ሲመልሱ
“የሰሜን ምስራቅ አፍሪካዊቷ ታሪካዊ ተገዳዳሪ ሀገር ግብጽ ጎረቤት መስፈሯ ቀላል ስትራቴጂካዊ አንድምታ ይኖረዋል ብየ አላስብም፡፡ ሶማሊያን የነካ አይኔን የነካ የሚመስለው የካይሮ መንግስት አካሄድ ኢትዮጵያ በቀጣይ በአካባቢው ወደብ ለማግኝት የምታደርጋቸውን ጥረቶች ለማሰናከል እንደማይተኛ መገመት ይቻላል፡፡
በዚህ መልኩ ኢትዮጵያ ከግጭት መልስ አቋሟን ለማስረዳት እና ጥቅሟን ለማስከበር ሰፊ ዝግጅት ማድረግ ያለባት ይመስለኛል፡፡ ይህ ደግሞ የሚጀምረው የእኛን ሀሳብ በሚገዙ ሌሎች የቀጠናው ሀገራት እና ድርጅቶች ላይ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ስራን በመስራት ነው” ባይናቸው፡፡
በተጨማሪም እነርሱ “በቀደዱት መንገድ” ላለመጓዝ እና ወደ ጦርነት የሚወስዱ መንገዶችን በተቻለ አቅም ለማስቀረት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሀገራቱ በቀጣይ በደረሱት ወታደራዊ ስምምነት መነሻም ሆነ በሌሎች አጀንዳዎች ጠብ አጫሪ ድርጊቶች ውስጥ የሚገቡ ከሆነ የኢትዮጰያ መንግስት ለዚህ የሚሰጠው ምላሽ የተጠና ሊሆን ይገባዋልም ተብሏል።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ዶክተር ዳርእስከዳር ታየ እንደሚሉት “ግብጽ ከሶማሊያ ጋር የደረሰችው ወታደራዊ ስምምነት እንዲሁም በሰላም አሰከባሪ ስም ጦሯን ወደ ሞቃዲሾ ለማስጠጋት መወሰኗ በአዲስ አበባ እና በካይሮ መካከል ያለውን የቆየ ተገዳዳሪነት እንዲሁም በጥርጣሬ የመታየየት አካሄድ በሶማሊያ ምድር በግልጽ እንዲታይ ያደረገ የእጅ አዙር ሽኩቻዎችንም ሊያስከትል የሚችል ነው”።
ዶክተር ዳርእስከዳር መፍትሄውን በተመለከተ ባነሱት ሀሳብ የውጭ ሀይሎች በኢትዮጵያ ላይ የሚበረቱት የውስጥ ሰላም ችግር ውስጥ በገባበት ጊዜ እንደሆነ አንስተው መንግስት የሀገር ውስጥ ሰላምን ማጽናት እና የህግ የበላይነትን ማስፈን ላይ የቤትስራዎች እንዳሉበት ጠቁመዋል።
ከዚህ ባለፈም የግብጽ ጦር በስፍራው መገኝት ባለፉት አመታት የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ሀይል ሲሰራው የነበረውን የጸረ ሽብር መከላከል ስራ አደጋ ውስጥ የሚከት መሆኑን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስረዳቱ ዙርያ ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራዎች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት።
አለፍ ሲልም ኢትዮጵያ በቱርክ አደራዳሪነት ከሶማሊያ መንግስት ጋር በጀመረችው ድርድር ልዩነቶችን ማጥበብ የሚቻልባቸው አጋጣሚዎች ካሉ እነርሱን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ሆኖም የወደብ ጉዳይ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ በመሆኑ ኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ ሳትገባ ጥቅሟን ማስከበር የምትችልባቸው አማራጮችን ማማተር ላይ ልትበረታ ይገባል ተብሏል።