ሶማሊያ አሁን እየሄደችበት ያለውን መንገድ ከቀጠለች ኢትዮጵያ ምን አይነት እርምጃ ልትወስድ ትችላለች?
ኢትዮጵያ በሶማሊያ የደረሱባትን ወረራ የምትረሳ ሀገር እንዳልሆነች የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ታዬ አጽቀስላሴ ገልጸዋል
ሚንስትሩ ሶማሊያ የአንድ ሀገር ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ለሌላ ሀገር ስጋት መሆን የለበትም የሚለውን መርህ እንድታከብር እንፈልጋለን ብለዋል
ሶማሊያ አሁን እየሄደችበት ያለውን መንገድ ከቀጠለች ኢትዮጵያ ምን አይነት እርምጃ ልትወስድ ትችላለች?
የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ታዬ አጽቀስላሴ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚንስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት የሶማሊያ መንግሥት ውስጥ ያሉ የተወሰኑ አካላት በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ስም ማጥፋት ስራ እየሰሩ ነው ብለዋል።
ሶማሊያ እንደ ሉዓላዊ ሀገር ከየትኛውም ሀገር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መመስረት መብቷ ቢሆንም "ይህ የሚሆነው ግን ለሌላ ሀገር ስጋት በማይሆን መልኩ ነው" ሲሉም ሚንስትሩ ተናግረዋል።
"በሶማሊያ ያለውን መንግሥት ያቋቋምነው እኛ ነን" ያሉት አምባሳደር ታዬ ይህን ያደረግነው አልሻባብ ስልጣን ቢይዝ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአካባቢው ሀገራት ስጋት እንደሚሆን ስለምናምን ነውም ብለዋል።
የሶማሊያ ሰላም እኛን ይመለከታል፣ ሰላም እንዲመጣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መስዋዕትነት ከፍሏል፣ አሁንም የሶማሊያ ሁኔታ የሚያሳስበን ድንበር ዘሎ የሚመጣ ትርምስን ስለማንፈልግ ነውም ብለዋል አምባሳደር ታዬ በመግለጫቸው።
"ኢትዮጵያ በንጉሱ እና በደርግ የአስተዳድር ጊዜ በሶማሊያ የደረሰባትን ወረራ አትረሳም፣ ህዝቦቿም ተላላ አይደሉም" ያሉት ሚንስትሩ ሀገሪቱ ዳግም የኢትዮጵያ ስጋት እንዳትሆን ጥረታችንን እንቀጥላለን ሲሉም ተናግረዋል።
ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ወቅታዊ አለመግባባት በዚሁ ከቀጠለ ኢትዮጵያ ምን አይነት እርምጃ ልትወስድ ትችላለች? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ሚንስትሩ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።
" ኢትዮጵያ ጥቅሟን ለማስከበር ሶማሊያዊያን ወደ ቀልባቸው እስኪመለሱ ድረስጉዳዩን በሰላም ለመፍታት ጥረቷን ከመቀጠል ውጪ የሀይል አማራጭ አትወስድም፣ ጉዳዩን ለመፍታት ሀይል መጠቀም ቢኖር ዞሮ ዞሮ ልዩነቱን ለመፍታት መጨረሻ ላይ ተቀምጦ መወያየት ስለሚያስፈልግ ከዲፕሎማሲ ውጪ ያሉ አማራጮችን አንጠቀምም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት መበላሸቱ የሀገሪቱ ዲፕሎማሲ ሽንፈት ውጤት ሊሆን አይችልም? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም "የሀገራት ፍላጎት ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል ፣ የፍላጎት አለመጣጣም በሀገራት መካከል ማጋጠሙ ተፈጥሯዊ ነው፣ ልዩነቱን ለመፍታት የሚደሩገው ጥረት ጥበብን ይጠይቃል" ሲሉ ተናግረዋል።
ሚንስትሩ በመግለጫቸው ላይ የየነሳላቸው ጥያቄ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው የወደብ ስምምነት እንዴት እየሄደ ነው? የሚለው ነው።
ሚንስትሩም በምላሻቸው ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ታከብራለች ነገር ግን ወጪ እና ገቢ የንግድ ፍላጎቶቻችንን እልባት ለመስጠት ወደብ ያስፈልገናል " ብለዋል።
"120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ የመታፈን አደጋ ተጋርጦባታል፣ ይህንን የመታፈን አደጋ ለመፍታት ወደብ የግድ ያስፈልገናል፣ የነበረንን ወደብ ማጣታችን ያስቆጫል፣ አሁን ግን ይሄንን አደጋ ለመቀልበስ ነው እየሰራን ያለነው" ብለዋል።