አቶ እስክንድር መንግስት አድርሶብኛል ያሉትን ጫና አልዘረዘሩም
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋ መንግስት እያደረሰብኝ ነው ባሉት ጫና ምክንያት በፓርቲው አመራርነትም ሆነ በአባልነት መስራት የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን አስታወቁ።
ፓርቲው፣በፕሬዝዳንቱ በአቶ እስክንድር የተጻፉ መግለጫ በፌስቡክ ገጹ አውጥቷል።
በመግለጫው አቶ እስክንድር “ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንድትሻገር ለዓመታት የበኩሌን አስተዋጽዖ" ሲያደርጉ እንደቆዩ እና አሁን ያለው ጫና ግን በፖለቲካ እንደከበዳቸው ገልጸዋል።
አቶ እስክንድር "ጨቋኝ" ነው ሲሉ በከሰሱት መንግስት ምክንያት "በአባልነትም ሆነ በአመራርነት መስራት የማልችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ” ብለዋል።
እስክንድር ነጋ “ካሉበት ለፓርቲው ፅፈውታል” በተባለው ደብዳቤ ሌላ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ አላሰፈሩም።
ይሁን እንጂ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፣ አባላት እና አመራሮች እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አምሃ ዳኘው ጋር በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም ፓርቲው ያካሄደዋል ተብሎ ለሚጠበቀው ጠቅላላ ጉባኤ ስኬት ያላቸውን ምኞት በደብዳቤው ገልፀዋል።
አቶ እክንድር መንግስት አድርሶብኛል ያሉትን ጫና አልዘረዘሩም።
አቶ እስክንድር በፓለቲካ ፖርቲ ውስጥ ከመንቀሳቀሳቸው በፊት በጋዜጠኝነት ሙያ ሰርተዋል፤ በኢህአዴግ መንግስት ለበርካታ አመታት ታስረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ከእስር የተለቀቁት አቶ እስክንድር በድጋሚ ታስረው መፈታታቸው ይታወሳል።