እነ አቶ እስክንድር ነጋ የምርጫ ዕጩ መሆናቸውን የሚገልጽ ሰርተፍኬት ሊሰጣቸው ነው
በእስር ላይ የሚገኙ የባልደራስ አመራሮች በምርጫ እንዲሳተፉ በፍርድ ቤት የታዘዘውን ትዕዛዝ እንደሚፈጽም ቦርዱ አስታውቋል
ምርጫ ቦርድ 3.5 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ አውጥቼ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እየፈጸምኩ ነው ብሏል
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራሮች በዘንድሮው ምርጫ እንዲሳተፉ ፍርድ ቤት የወሰነውን ውሳኔ እንደሚያስፈጽም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራሮች አቶ እስክንድር ነጋ ፣ ስንታየሁ ቸኮል ፣ ቀለብ ስዩም እና አስካለ ደምሴ በዕጩነት እንዲመዘገቡ ውሳኔ መስጠቱ ይታወቃል፡፡ ይህን ውሳኔ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምን መፈጸም እንዳልቻለ ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 26 ቀን 2013 ዓ.ም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳ በታዘዘው መሰረት አብራርቷል፡፡
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ምርጫ ጉዳዮች ችሎት ቀርበው ለፍርድ ቤቱ ያብራሩት የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ ፣ ተቋማቸው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የመፈጸም ችግር እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ፣ ቦርዱ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራሮች ለምርጫ ዕጩ መሆናቸውን የሚገልጽ ሰርተፍኬት እንዲሰጣቸው አዟል፡፡ ምርጫ ቦርድም 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተጨማሪ ወጪ አውጥቼ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እየፈጸምኩ ነው ብሏል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ፣ ሰርተፍኬቱን በነገው ዕለት አርብ ግንቦት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ቦርዱ ለዕጩዎቹ እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡