ባልደራስ እነ እስክንድር ነጋ ያለመከሰስ መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲለቀቁ ጠየቀ
ፍ/ቤቱ ዐቃቤ ሕግ በአቤቱታው ላይ መልስ እንዲሰጥ ለዓርብ ሰኔ 4 ቀን 2013 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱንም ነው ፓርቲው ያስታወቀው
ባልደራስ ታሳሪዎቹ በምርጫው እጩ ሆነው መመዝገባቸውን በማስታወስ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲከበር ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ከፍተኛ አመራር እና ዕጩዎቹ ያለመከሰስ መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲለቀቁ ጠየቀ፡፡
ባልደራስ ፕሬዝዳንቱን አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ አስቴር ስዩም፣ ስንታየሁ ቸኮል እና አስካለ ደምሴ በ6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ እጩ ሆነው መመዝገባቸውን በማስታወስ ያለመከሰስ መብታቸው ተከብሮ ከእስር እንዲለቀቁ ጠየቀ ለፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡
በምርጫ እጩ ሆኖ የቀረበ ሰው እጅ ከፍንጅ በከባድ ወንጀል እስካልተያዘ በስተቀር ያለመከሰስ መብት አለው ያሉት የፓርቲው የሕግና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሄኖክ አክሊሉ በአቤቱታው ላይ ዐቃቤ ሕግ መልስ እንዲሰጥበት ፍርድ ቤቱ ለከነገ ወዲያ ዓርብ ሰኔ 4 ቀን 2013 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡
አቶ ሄኖክ አክሊሉ (በስተግራ ያሉት) በትናንትናው የፓርቲው መግለጫ
አቶ ሄኖክ የተከሳሾቹ አሁናዊ የግል ሁኔታ (Status) የተለወጠ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የዋስትና መብታቸው በድጋሚ ታይቶ እንዲፈቀድ ለፍርድ ቤቱ ባስገቡት አቤቱታ መጠየቃቸውን ከፓርቲው ማህበራዊ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከመጪው ምርጫ ለማስተጓጎል በማሰብ ተከሳሾቹ እንዲታሰሩ መደረጉን የሚያትተው አቤቱታው መፈታታቸው ለምርጫው ፍትሃዊ፣ ሠላማዊ፣ ነፃ እና ዲሞክራሲያዊነት ጉልህ ሚና አለው ብሏል፡፡
እጩ ከሆኑ በኋላ በእሥር እንዲቆዩ የሚያስገድድ ክስ ባለመቅረቡ የምርጫው ጊዜ አልፎ ውጤቱ እስኪታወቅ ድረስ ተከሳሾች በእስር ሆነው ጉዳያቸው ሊቀጥል አይገባምም ሲሉም ነው አቶ ሄኖክ በአቤቱታው የጠየቁት፡፡
ይህ ካልሆነ ተከሳሾቹ እሥር ላይ ሆነው እጩ ተወዳዳሪ ቢሆኑ መሠረታዊ የሕግ መፋለስ እንደሚያስከትል በመጠቆምም ከእስር ውጪ ሆነው ጉዳያቸውን መከታተል እንዲችሉ ትእዛዝ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡