በኬንያ 42 ሴቶችን በመግደል ተጠርጥሮ በእስር ላይ የነበረው ግለሰብ ከእስር ቤት ማምለጡ ተነገረ
ከግለሰቡ በተጨማሪ 12 በህግ ወጥ መንገድ ወደ ኬንያ የገቡ 12 ኤርትራውያን ከፖሊስ ማምለጣቸው ተነግሯል
ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የአደን ስራ ጀምሯል
በኬንያ ሚስቱን ጨምሮ 42 ሴቶችን ገድሏል በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበረው ተጠርጣሪ ከእስር ቤት ማምለጡ ተነገረ፡፡
በናይሮቢ የቆሻሻ መጣያ ስፍራ ላይ የሰውነት አካላቸው የተቆራረጠ የ6 ሴቶች አስክሬን በቆሻሻ ከረጢት ውስጥ መገኘቱን ተከትሎ ግለሰቡ በፖሊስ ተይዞ የፍርድ ሂደቱን በመከታተል ላይ ነበር፡፡
በወቅቱ በመላው ኬንያ ድርጊቱ ቁጣን ቀስቅሶ የነበረ ሲሆን በማህበራዊ ሚድያዎች ኬንያውያን ጥፋተኛው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ሰፊ ቅስቀሳ ሲያደርጉ እንደነበርም ይታወሳል፡፡
ኮሊንስ ጁማይሲ የተባለው ግለሰብ በፖሊስ ከተያዘ በኋላ ሴቶችን እየመረጠ ከ2022 ጀምሮ ሲገድል እንደነበር ቃሉን የሰጠ ቢሆንም ፍርድ ቤት በቀረበበት ጊዜ ድርጊቱን እንዳልፈጸመ ተናግሯል፡፡
የተጠርጣሪው ጠበቃ ግለሰቡ ሴቶችን ስለመግደሉ ለፖሊስ ያመነው በደረሰበት የምርመራ ማሰቃየት ነው ሲል ገልጿል፡፡
የፖሊስ ቃል አቀባይ ርሲላ ኡንያንጎ እንደተናገሩት ግለሰቡን ጨምሮ በህ ገወጥ መንገድ የገቡ 12 ኤርትራውያን ትላንት አነጋጉ ላይ ጊጊሪ ከተባለው የፖሊስ ጣብያ እስር ቤት ማምለጣቸውን ተናግረዋል፡፡
እስረኞቹ ማለዳ ላይ የታሳሪዎች ቆጠራ በሚከናወንበት ጊዜ እንዳመለጡ ፖሊስ ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ፖሊስ አስራ ሶስቱን ከህግ ያመለጡ ሰዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል ሰፊ አደን እና አሰሳ እያደረገ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ያልተለመዱ እንቅስቃሴዎችን ሲመለከቱ ለፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
ኮሊንስ ጆማይሲ የተባለው የ33 አመት ኬንያዊ ባሳለፍነው ሀምሌ ላይ የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ እየተመለከተ በሚገኝብት ወቅት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ግለሰቡ ለመጨረሻ ጊዜ ከገደላቸው ሴቶች መካከል ከአንዷ ጋር ባደረገው የሞባይል ገንዘብ ልውውጥ ፖሊስ ባደረገው ማጣራት ሊያዝ ችሏል፡፡
አስክሬኖቹ ከተገኙበት አካባቢ 100 ሜትር ርቀት ላይ የሚኖር ሲሆን ፖሊስ በመኖርያ ቤቱ ውስጥ ባደረገው ፍተሻ 10 ሞባይል ስልኮችን ፣ ላፕቶፕ ፣ የሴቶች አልባሳት እና መታወቂያዎችን አግኝቷል፡፡
በተጨማሪም የተለያየ መጠን ያላቸው የስለት መሳርያዎች እና የሟቾችን አስክሬን ከቆራረጠ በኋላ የሚጥልባቸውን በርካታ ከረጢቶች እንደተገኙ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ሟቾቹ ከ18 እስ 30 እድሜ የሚጠጉ ሴቶች ሲሆኑ ሁሉም የተገደሉበት መንገድ አንድ አይነት ተብሏል፡፡