አረብ ኤሜሬትስ ሩሲያ እና ዩክሬን የእስረኞች ልውውጥ እንዲያደርጉ ማሸማገሏ ተገለጸ
ሀገሪቱ በስድስት ድርድሮች በአጠቃላይ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ እስረኞችን እንዲለዋወጡ አስችላለች
አቡዳቢ በሁለቱ ሀገራት ዘንድ የገነባችውን እምነት ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም የሚደረጉ ድርድሮችን ለማስተባበር እንደምትጠቀምበት አስታውቃለች
አረብ ኤሜሬትስ በጦርነት ውስጥ የሚገኙት ሩስያ እና ዩክሬን የእስረኞች ልውውጥ እንዲያደርጉ ስኬታማ የማሸማገል ስራ ማከናወኗ ተገለጸ፡፡
በሀገራቱ መካከል ስድስት የድርድር መድረኮችን በማስተባበር በአጠቃላይ 1558 እስረኞችን እንዲቀያየሩ አቡዳቢ ከፍተኛ ሚና እንደነበራት ነው ተናግሯል፡፡
በቅርቡ በሁለቱም በኩል የነበሩ 190 የጦር እስረኞች መለቀቃቸውን ያስታወቀው አረብ ኤሜሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ድርድሩ የተቃና መሆኑን ገልጾ፣ ሁለቱም ሀገራት ላሳዩት ትብብር ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን ለመጨረሻ ጊዜ እስረኛ ከተቀያየሩ ከአንድ ወር በኋላ ያደረጉት አዲስ የእስረኞች ልውውጥ ሂደት ዩኤኢ በሁለቱም ሀገራት በኩል ባላት ገለለተኛ አቋም የመሰረተችውን እምነት የሚያሳይ ነውም ተብሏል፡፡
በቀጣይም ሀገራቱ ከሚገኙበት ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲወጡ እና ወደ ዘላቂ ጦርነት ማቆም ድርድር ይቀርቡ ዘንድ አቡዳቢ የገነባቸውን እምነት እንደምትጠቀምበት በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መስርያ ቤቷ በኩል ባወጣችው መግለጫ አስታውቃለች፡፡
ሚንስቴሩ አክሎም ሞስኮ እና ኬቭ የሚገኙበት ጦርነት እንዲያበቃ ሰላማዊ ውይይቶች ቀዳሚ አማራጭ መሆናቸውን ገልጾ፣ ሀገራቱ በግጭት ቅነሳ እና የጦርነት ማቆም ውይይቶች ላይ እንዲነጋገሩ ጥረቱን እንደሚቀጥል ነው ይፋ ያደረገው፡፡
አረብ ኢምሬትስ 2024 ከገባ ጀምሮ ሁለቱ ሀገራት የእስረኞች ልውውጥ እንዲያደርጉ ስታሸማግል ይህ ለስድስተኛ ጊዜ ነው፡
በተጨማሪም ሀገሪቱ በ2022 በአሜሪካ እና ሩስያ መካከል የእስረኞች ልውውጥ እንዲደረግ በተመሳሳይ ስኬታማ የማሸማገል ስራ መስራቷ ይታወሳል፡፡