ሱዳን ከሰሞኑ ጦሯን ወደ ድንበር እንዳስጠጋች ማስታወቋ የሚታወስ ነው
የኢትዮ-ሱዳን ድንበር የጋራ ኮሚቴ ነገ እንደሚሰበሰብ የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ትናንት ለኢጋድ 38ኛ ልዩ ስብሰባ ጅቡቲ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ እና የሱዳኑ አቻቸው አብደላ ሃምዶክ ከጉባዔው ጎን ለጎን ባካሄዱት ውይይት በድንበር የማካለሉ ጉዳይ ለመነጋገር ተስማምተዋል ያለው ቢሮው የጋራ ኮሚቴው ነገ ተሰብስቦ እንዲመክር ስለመስማማታቸው አስታውቋል፡፡
ከአሁን ቀደም (ባሳለፍነው ዓመት ወርሃ ሰኔ ላይ) በአዲስ አበባ ምክክር ተደርጎ ነበር፡፡ በቀጣዩ ወር በካርቱም ለመነጋገር የተያዘው ቀነ ቀጠሮ ግን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
የነገው የጋራ ድንበር ኮሚቴው ስብሰባ የሚሳካ ከሆነ ሱዳን ጦሯን ሃገራቱ ወደሚጋሩት ድንበር ማስጠጋቷ እና የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች ራስን የመከላከል አጸፋዊ ምላሽ መስጠታቸው በተሰማ ሰሞን የተካሄደ የመጀመሪያው ስብሰባ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ እና ሱዳን ዓመታትን የተሻገረ ጠንካራ የጉርብት እና ወንድማማች ግንኙነት አላቸው፡፡ በህዝቦቻቸው መካከል ያለው ግንኙነትም በመልካምነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡
1 ሺ 600 ገደማ ኪሎሜትሮችን የሚዘልቅ ረዥም ድንበርን ይጋራሉ፡፡ ይህ ድንበር ሃገራቱን የበለጠ ቢያቀርብም ሳይካለል መቆየቱ ግን ለተደጋጋሚ ግጭቶች በመንስዔነት ይጠቀሳል፡፡ በተለይ በእርሻ ጊዜያት መካረሩ እና ግጭቱ የተለመደ ነው፡፡ ዛሬም ያጋጠመው እንዲህ ዓይነቱ ችግር ነው፡፡
በአጼ ሚኒሊክ የንግስና ዘመን ሱዳንን ቅኝ ስትገዛ ከነበረችው እንግሊዝ ጋር በመደራደር ድንበሩን ለማካለል እና የመጨረሻ እልባት ለመስጠት ጥረት ተደርጎ ነበር፡፡ ይህ የሆነው እ.ኤ.አ በ1902 ግድም ነው፡፡ ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች አልተሳካም፡፡
የወቅቱ የግብጽ ቅኝ ገዢ እንግሊዝ ጣናን በመያዝ የዐባይን ምንጭ የመቆጣጠር ጽኑ ፍላጎት እንደነበራት ይነገራል፡፡ በአንድ ወቅት ከአል ዐይን አማርኛ ጋር የስልክ ቆይታ የነበራቸው የታሪክ መምህሩ እና ተመራማሪው አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር) ይህንኑ አስረግጠውልናል፡፡
ከሰሞኑ ጦሯ በኢትዮጵያ ታጣቂዎች መጠቃቱን የገለጸችው ሱዳን አል ፋሽቃ ወደሚባለው የድንበር አካባቢ ጦሯን ስለማስጠጋቷ የሱዳን ዜና አገልግሎት ዘግቦ ነበር፡፡
አል ፋሽቃ ሁለቱም በይገባኛል ደጋግመው የሚወዛገቡበት ግጭትም የሚያጋጥምበት ለም የድንበር አካባቢ ነው፡፡
ይህ የሱዳን ጦርን የማስጠጋት ድርጊት ብዙዎች በጥርጣሬ እንዲመለከቱት ምክንያት ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ ከህወሓት ጋር በተያያዘ በህግ ማስከበር እርምጃ ላይ ባለችበት በዚህ ወቅት የተደረገ ጸብ አጫሪ ድርጊት ነው በሚልም ብዙዎች ይወቅሳሉ፡፡
ጦሩ ያጣውን ህዝባዊ ድጋፍ ለማስመለስ ያደረገው ነው በሚል የሚናገሩም አሉ፡፡ ከአሁን ቀደም ተወስደው ያልተመለሱ የሱዳን መሬቶችን አስመለስኩ በሚል አንዳች ፖለቲካዊ ትርፍን ለማግኘት በማሰብ ያደረገው ነውም ይባላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግስታቸው ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው እንደሚገኝ እና ችግሮቹ በውይይት እንደሚፈቱ ከሰሞኑ አስታውቀዋል፡፡
የሱዳን ድርጊት በሃገሪቱ አመራር ደረጃ እየተደረገ ነው ብሎ ለማለት ያስቸግራል ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በታኞቹ እርከኖች ባሉት ሚሊሻዎች እና ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ የመግባት የአርሷደሩን መሬት የመያዝ እና በአካባቢው ህገ ወጥ ስራ መፈጸም ነገር ነው የታየው ሲሉ መናገራቸውም ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ወገን ይሔን ተከላክሏልም ነው ያሉት ቃል አቀባዩ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፡፡
ሁኔታው ለሱዳንም ሆነ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም አይደለም ያሉም ሲሆን በአካባቢው ክፍተት ለመፍጠር እያንዣበቡ የሚገኙ ግብጽን መሰል ኃይሎች ጉዳዩን እያራገቡት እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡