የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች ወደ ሱዳን ግዛት ገብተው ጥቃት መፈጸማቸውን የሱዳን ጠ/ሚኒስትር አረጋገጡ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሀገሪቱ ጦር ጋር ተመሳሳይነት ያለው መግለጫ አውጥተዋል
ጠ/ሚ አብደላ ሃምዶክ በጥቃቱ የሰዎች ህይወት ማለፉን እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱንም ገልጸዋል
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በሱዳን ወታደሮች እና “በኢትዮጵያ ሚሊሻዎች” መካከል በተፈጠረው ግጭት ላይ ያተኮረ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በመግለጫቸው የሀገሪቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከስድስት ሳምንት ገደማ በፊት በእህት ሀገር ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ሁኔታ በጥንቃቄ እና በትኩረት መከታተሉን እንደቀጠለ አንስተዋል፡፡
“ሀገራችን ምስራቃዊ ድንበሯን አቋርጠው የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ተቀብላለች” ያሉት ጠ/ሚኒስትር ሃምዶክ “ህዝባችን በአስቸጋሪ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም በሚታወቅ ልግስናው አስተናግዷቸዋል” ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ማክሰኞ ታህሣሥ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ የሱዳን ወታደሮች በ ‘ጃባል አቡጢዩር’ አካባቢ ቅኝት አድርገው ሲመለሱ “ወደ ሱዳን ግዛት ገብተው አድፍጠው በነበሩ የተወሰኑ የኢትዮጵያ ሚሊሺያዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል” ብለዋል፡፡ በዚህም ጥቃት የሰዎች ህይወት መጥፋት እና የንብረት ጉዳት መድረሱን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከጦሩ ጎን መሆኑን እና ድጋፍ እንደሚያደርግም የገለጹት ሲሆን የሱዳን ታጣቂ ኃይሎች የሀገሪቱን ዳር ድንበር የመጠበቅ እና ማንኛውንም ጥቃት የመከላከል አቅም እንዳለው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ጉዳት ለደረሰባቸውም መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
ትናንት ምሽት የሱዳን ጦርም ባወጣው መግለጫ እንዲሁ ፣ በኢትዮጵያ ሚሊሻዎች ጥቃት ተፈጽሞበት የሰዎች ህይወት ማለፉን እና ሌሎች ጉዳቶችም መድረሳቸውን አስታውቋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ቀናት በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አካባቢ አለመረጋጋት ስለመኖሩ የተለያዩ መረጃዎች ቢወጡም ሁለቱም ሀገራት በይፋ ችግሮች ስለመኖራቸው ሳይገልጹ ቆይተዋል። በሱዳን በኩል በሀገሪቱ ጦር እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለቀረበው ወቀሳ በኢትዮጵያ በኩል ወዲያው የተሰጠ ምላሽ የለም።
አል ዐይን ዜና ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያን መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ጥረት እያደረገ ነው፡፡
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ባለፈው እሁድ በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ከተነጋገሩባቸው ጉዳዮች የድንበር ጉዳይ አንዱ ነው።