የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችን መልሶ መመዝገብ የሚያስችል ስርዓት እንዲዘረጋ ወሰነ
የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ሲፈልጉ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ለመመዝገብ የሚያስችል ስርዓት አልነበረም
ምክር ቤቱ ውሳኔው ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ሲፈልጉ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ለመመዝገብ የሚያስችል ስርዓት እንዲዘረጋ ወሰነ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።
በዚህም ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በቀረበ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ከህጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ የቆዩ የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ እነዚህን አካላት ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ለመመዝገብ የሚያስችል ስርዓት በነባሩ አዋጅ ላይ አልተካተተም።
የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ መልሶ መመዝገብ የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት ረቂቅ የአዋጅ ማሸሻያ ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲሆን፤ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
- ምርጫ ቦርድ ለህወሓት ህጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያሰችል የህግ አግባብ የለም አለ
- የምርጫ ቦርድ ውሳኔ "የሰላም ስምምነቱን የሚፈታተን" ነው ሲል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቃወመ
ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም ለህወሓት ህጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያሰችል የህግ አግባብ ባለመኖሩ ህወሓት ያቀረበውን የህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ጥያቄ አለመቀበሉ ይታወሳል።
ለቦርዱ ውሳኔ ምክንያት የሆነው ኃይልን መሰረት ያደረገ የአመጽ ተግባር አሁን ባይኖርም እንደገና ህጋዊ ሰውነቱን ለፓርቲው ለመመለስ የሚያችሉ ድንጋጌዎች በአዋጅ 1662/2011 ተደንግጎ ባለመገኘቱ ነው ቦርዱ በወቅቱ ውሳኔውን ያሳለፈው።
ምርጫ ቦርድ ህወሓት ያቀረበውን የህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ጥያቄ በህግ አግባብ እንደማይቀበለው በመግለጽ፤ ህወሓት ህጋዊ ሰውነት የሚያገኘው በድጋሚ ለመመዝገብ ጥያቄ ሲያቀርብ እና ቦርዱ ሲፈቅድ ነው ማለቱም አይዘነጋም።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው እለት ውሳኔ ያሳለፈበት የፖለቲካ ፓርቲዎችን መልሶ መመዝገብ የሚያስችል ስርዓት እንዲዘረጋ የሚያስችለው ረቂቅ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ከጸደቀ ህወሓት ያቀረበውን የህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ጥያቄ ምለሽ ሊያገኝ ይችላል።
በሌላ ዜና የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው መደበኛ ስብሰባው በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የንብረት ማስመለስ አዋጅ ላይ የተወያየ ሲሆን፤ በተለያዩ አዋጆች ውስጥ ተበታትነው ያሉትን የንብረት ማስመለስ እና አስተዳደር ድንጋጌዎች በአንድ ወጥ ሕግ ውስጥ በማካተት ለአፈጻጸም ምቹ የሆነ ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
በህገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አድርጎ ስለማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የተወያየው ምክር ቤቱ፤ በረቂቅ አዋጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።
ምክር ቤቱ የተወያየው የነዳጅ ውጤቶችን የግብይት ሥርዓት ለመደንገግ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይም ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።