በ2023 አገልግሎት የሚጀምሩ የሩሲያ ሚሳኤሎች የትኞቹ ናቸው?
ሩሲያ በፈረንጆቹ የካቲት 23 የሀገሪቱንን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ የተዋደቁ ዜጎቿን አስባ ትውላለች
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዚሁ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግርም የሩሲያ ጦር አዳዲስ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች ይታጠቃል ብለዋል
ሩሲያ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ልማቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ በፈረንጆቹ የካቲት 23 የሚከበረውን “የአባት ሩሲያ ጀግኖች” ቀን በማስመልከት ባደረጉት ንግግር የሩሲያ ጦር በ2023 ዘመናዊ ሚሳኤሎችን ይታጠቃል ብለዋል።
አብዛኛው ንግግራቸው በወታደራዊ ጉዳዮች ያተኮረው ፕሬዝዳንቱ፥ በዚህ አመት “ኪንዝሃል” የተሰኘው ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤልን በስፋት ጥቅም ላይ እንደሚውል ተናግረዋል።
- ሩሲያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመቀነስ ከአሜሪካ ጋር ደርሳ ከነበረው ስምምነት መውጣቷን አስታወቀች
- ሩሲያ የፕሬዝዳንት ባይደንን የዩክሬን ጉብኝት “ቴአትር” ነው ስትል አጣጣለች
ከአየር ወደ ምድር የሚወነጨፈው “ኪንዝሃል” እስከ 2 ሺህ ኪሎሜትር ድረስ ተመዘግዝጎ የጥላት ኢላማን መምታት የሚችል ነው።
የጦር መርከቦች ማደባያው “ዚርኮን” ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤልም በ2023 ጥቅም ላይ እንደሚውል ነው ያነሱት።
ኔቶ “ሰይጣን 2” እያለ የሚጠራው “አር ኤስ 28 ሳርማት” አህጉር አቋራጭ ሚሳኤልም ለመጀመሪያ ጊዜ ስራ ላይ መዋል እንደሚጀምር አብራርተዋል።
211 ቶን የሚመዝነው “ሳርማት” ሚሳኤል፥ በደርዘን የሚቆጠሩ የኒዩክሌር አረሮችን መሸከም የሚችል ሲሆን በአንድ ጊዜ ከተማን ማጥፋት እንደሚችል ተነግሮለታል፤ በአንድ ጊዜም የተለያዩ ኢላማዎችን መምታት የሚያስችል ነው።
“ሳርማት” ከ10 ሺህ ኪሎሜትር ድረስ ጥቃት ማድረስ የሚችል በመሆኑም አሜሪካንም ሆነ ሌላውን የአለም ክፍል ማጥቃት ይችላል ብሏል ሲ ኤን ኤን።
በ2017 ተሞክሮ ውጤታማነቱ የተረጋገጠው ይህ ሚሳኤል በዚህ አመት ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተነግሯል።
ፑቲን “ሳርማት”ንም ሆነ ሌሎቹ ሚሳኤሎች በዩክሬኑ ጦርነት እንደሚውሉ ባይናገሩም መልዕክቱ ለምዕራባውያን ግልጽ ነው ተብሏል።
ፕሬዝዳንቱ ሩሲያ በዚህ አመት የኒዩክሌር አቅሟን ይበልጥ የምታሳድግበት ነው ማለታቸውም የሞስኮ እና ምዕራባውያንን ውጥረት እንደሚያንረው ነው የሚጠበቀው።
የሩሲያ ፓርላማ (ዱማ) በትናንትናው እለት ከአሜሪካ ጋር በ2010 ተደርሶ የነበረው የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎች የመቆጣጠር ስምምነት እንዲቋረጥ ወስኗል።
ስምምነቱ ሀገራቱ ሊኖራቸው የሚችለውን የኒዩክሌር አረር ገደብ ያበጀና ያልተገባ እሽቅድምድም እንዳይፈጠር የሚያደርግ እንደነበር ሬውተርስ አስታውሷል።
ዋሽንግተን “አለም አቀፉን ውጥረት ለማርገብ በጎ ፍላጎት” ካሳየች ውሳኔዬን ልቀለብስ እችላለሁ ያለችው ሞስኮ፥ በ2023 ጥቅም ላይ ልታውላቸው ያዘጋጀቻቸውን የጦር መሳሪያዎች ይፋ አድርጋለች።
ለዩክሬኑ ጦርነት ሙሉ በሙሉ ምዕራባውያኑን ተጠያቂ ያደረጉት ፑቲን፥ ሶስት ግዙፍ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎቻችን የሩሲያ ጦር መጠቀም ይጀምራል ማለታቸውም የኒዩክሌር ጦርነት ይጀመር ይሆን የሚለውን ስጋት አንሮታል።
ሶስቱ ኒዩክሌር የታጠቁ ሀገራት (አሜሪካ፣ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ) በኬቭ ጎራ ሆነው ሞስኮን በእሳት ከመጫወት እንድትቆጠብ እያሳሰቡ ነው።